New to site?


Login

Lost password? (X)

Already have an account?


Signup

(X)
Farooq

ቡና ባንክ ለመምህራንና ለጤና ባለሙያዎች አዲስ የቁጠባ አገልግሎት ይፋ አደረገ

HomeNewsቡና ባንክ ለመምህራንና ለጤና ባለሙያዎች አዲስ የቁጠባ አገልግሎት ይፋ አደረገ
12
Mar
ቡና ባንክ ለመምህራንና ለጤና ባለሙያዎች አዲስ የቁጠባ አገልግሎት ይፋ አደረገ
 • Author
  Genet Fekade
 • Comments
  0 Comments
 • Category
 • ለቁጠባ አገልግሎቱ ተሳታፊዎች ሽልማት ተዘጋጅቷ

ቡና ባንክ  ለመምህራን እና ለጤና ባለሙያዎች አዲስ የቁጠባ ሽልማት መርሃ ግብር በይፋ ጀመረ።

በሁሉም ደረጃ ላይ የሚገኙ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች ተካፋይ በሚሆኑበት በዚህ አዲስ የቁጠባ መርሃ ግብር ላይ ለሚሳተፉ ደንበኞቹ  ባንኩ የተለያዩ ሽልማቶችንም አዘጋጅቷል።

ሃገር ጤናማ ስርዓት ገንብታ ወደዕድገት የምታመራው አንድም በዕውቀት የታነጸ ፣ በሌላ በኩልም ጤናው የተጠበቀ ትውልድ ሲኖራት ነው። ትውልድን በእውቀት የማነጽ እና የህዝብን ጤና የመጠበቅን ከባድ ሃላፊነት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚሸከሙ ምሰሶዎች ደግሞ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች መሆናቸውን ቡና ባንክ ያምናል።

ብዙ ነገር ባልተመቻቸበት ፣ አድካሚ በሆነ ነገር ግን ቁርጠኝነትን በሚጠይቅ ስፍራ ሁሉ ተገኝተው ትውልድንና ሃገርን ለማስቀጠል የሚተጉት እነዚህ የሃገር ባለውለታዎች አንድም የቁጠባ ባህላቸውን እያሳደጉ የባንኩ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፣ በሌላ በኩልም በመቆጠባቸው ብቻ ተሸላሚ መሆን የሚችሉበት  መርሃ ግብር ነው የተዘጋጀው።

በዚህ የቁጠባ አገልግሎት ላይ ለመሳተፍ ማናቸውም በመምህርነት ሙያ ላይ የተሰማሩና ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ የሚያገለግሉ መምህራን ፣ እንዲሁም በትምህርት አስተዳደርና ድጋፍ ስራዎች ላይ የሚገኙ ሁሉ ብቁ ናቸው።

በተመሳሳይም በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ ነርሶች፣ የጤና መኮንኖችና ጤና ረዳቶች፣ የማህበረሰብ ጤና ባለሙያዎች፣ የህክምና ዶክተሮች፣ ራዲዮሎጂስቶች እንዲሁም ከህክምና ሙያ ጋር ተያያዠነት ያላቸው ስራዎችን የሚያከናውኑ እና በህክምና ተቋማት ውስጥ በድጋፍ ሰጪነት የሚያገለግሉ ባለሙያዎች ሁሉ የዚህ የቁጠባና ሽልማት መርሃ ግብር ተሳታፊ ለመሆን ብቁ ናቸው።

በቁጠባ አገልግሎቱ ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎች ቁጠባውን እንደጀመሩ ተሸላሚ የሚያደርጋቸውን የዕጣ ቁጥር የሚቀበሉ ሲሆን ከ 400 ብር ጀምሮ መቆጠብ ለሽልማቱ ብቁ ያደርጋል። የባለሙያዎቹ የቁጠባ መጠን ባደገ ቁጥርም ዕድለኛ የሚያደርጋቸው ዕጣ ቁጥሮች መጠን በዚያው ልክ የሚያድግ ይሆናል።

ባንኩ በቀጣይ የሚያካሂደው ይኸው ይቆጥቡ ይሸለሙ ፕሮግራም ሲጠናቀቅ ያዘጋጃቸውን ሽልማቶች በብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ድርጅት ውስጥ  በይፋዊ ስነስርዓት ዕጣ በማውጣት አሸናፊዎቹን ያሳውቃል።

በዚህ መሰረት ለሽልማት የተዘጋጁት አንድ ዘመናዊ 2020 ሞዴል ሱዙኪ ዲዛየር መኪና ፣ 12 ዘመናዊ ላፕቶፖችና 12 ታብሌቶች  እንዲሁም 24 ስማርት የሞባይል ስልክ ቀፎዎች፣ ስድስት  የእረፍት ጊዜ ሽርሽር ሙሉ ወጪ የተሸፈነላቸው የታሪካዊ ቦታዎች ጉብኝት ፓኬጆች ለአሸናፊዎቹ ይተላለፋሉ።

ቡና ባንክ  አ.ማ ከ11 ዓመታት በፊት የተቋቋመና ከ275 በላይ በደረሱ ቅርንጫፎቹ በኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ የግል ባንክ ሲሆን ከ13ሺህ በላይ በሆኑ ባለአክሲዮኖች ባለቤትነት የሚተዳደርና በሃገሪቱ ከሚገኙ ባንኮች ውስጥ የብዙሃን ባንክ ተብሎ በመጠራት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ የግል ባንክ ነው።

ባንኩ ከ 1.1 ሚሊዮን በላይ ለደረሱ ደንበኞቹ ቀልጣፋ የባንክ አገልግሎት በመስጠትና በየጊዜው አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት በብዙ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ተዓማኒነትን ያተረፈ ባንክ ሲሆን ከሚለይባቸው ተግባራት አንዱና ዋናው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያማከለ፣ ፍላጎትና አቅማቸውን ያገናዘበ የልዩ ቁጠባና ብድር አገልግሎቶችን ማመቻቸቱ እንዲሁም ዘመኑን የዋጁ የዲጂታል ቴክኖሎጆዎችን ለደንበኞቹ ቅርብ ማድረጉ ነው።

ከነዚህ መካከል ላለፉት ዓመታት ተግባራዊ ያደረገው  የ ታክሲና ባጃጅ አሽከርካሪና ባለቤቶች ልዩ የቁጠባ ሂሳብ ተጠቃሹ ሲሆን ይህ ፕሮግራምም በርካታ ደንበኞችን በማፍራት የብዙሃኑን ህይወት መለወጥ ያስቻለ መሆኑ በደንበኞቹ  ተመስክሮለታል።

Tags:

  እጩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትን ጥቆማ ለመቀበል የወጣ ማስታወቂያ

  የቡና ባንክ አ.ማ የቦርድ አባላት ምርጫ የሚከናወነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመሪያ ቁጥር SBB/79/2021 እና SBB/71/2019 እንዲሁም በኩባንያው ባለአክሲዮኖች 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በጸደቀው የቦርድ አባላት ጥቆማና ምርጫ አፈጻጸም የአሠራር ደንብ መሠረት ነው፡፡ እነዚህን መመሪያዎች መሠረት በማድረግ በቀጣይ ባንኩን በቦርድ አባልነት የሚመሩ አባላትን ለማስመረጥ ታህሳስ 11 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው የባለአክሲዮኖች 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የቦርድ አባላት አስመራጭ ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ በጠቅላላ ጉባኤው የተቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ እጩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጥቆማዎችን ለመቀበል ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡

  ስለሆነም ባለአክሲዮኖች ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት ብቁ ናቸው ብላችሁ የምታምኑባቸውን እጩ የቦርድ አባላት ለመጠቆም የሚያስችላችሁን የጥቆማ መሙያ ወይም ማስፈሪያ ቅጽ በቡና ባንክ አ.ማ ድረ ገጽ https://www.bunnabanksc.com ወይም የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኝበት ቦሌ መንገድ ሩዋንዳ መታጠፊያ አካባቢ ባለው የቡና ባንክ አ.ማ ሕንፃ 8 ፎቅ በሚገኘው የዳይሬክተሮች ቦርድ አስመራጭ ኮሚቴ ጽ/ቤት ቢሮ ወይም በባንኩ ቅርንጫፎች በአካል በመቅረብ ለጥቆማ መስጫ የተዘጋጀውን ቅጽ ማግኘት የምትችሉ መሆኑን አስመራጭ ኮሚቴው ያሳውቃል፡፡

  ስለሆነም የባንኩ ባለአክሲዮኖች ለባንኩ ሁለንተናዊ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ ብለው የሚያምኑባቸውን ብቁ እጩዎችን በቅጹ ላይ በጥንቃቄ በመሙላት ከሐምሌ 01 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 01 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ከታች በተመለከቱት አማራጮች በመጠቀም እንዲጠቁሙ አስመራጭ ኮሚቴው በአክብሮት ይጋብዛል፡፡

  ባለአክሲዮኖች የሞሉትን ቅጽ በቡና ባንክ አ.ማ ዋና መ/ቤት 8ኛ ፎቅ በዳይሬክተሮች ቦርድ አስመራጭ ኮሚቴ ጽ/ቤት በአካል በመቅረብ ቅጹን መሙላት ወይም አድራሻውን ለቡና ባንክ አ.ማ የዳይሬክተሮች ቦርድ አስመራጭ ኮሚቴ በማለት በባንኩ የፓ.ሣ.ቁጥር 1743 ኮድ 1110  በአደራ ደብዳቤ መላክ ወይም የተሞላውን ቅፅ ስካን በማድረግ ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጀው በባንኩ ኢሜል bibnomination@bunnabanksc.com አያይዘዉ መላክ የሚችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  ተጠቋሚ እጩ የቦርድ አባላት የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፤

  1. ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሆነ/ች እንዲሁም ዕድሜው/ዋ 30 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆነ/ች፤
  2. የቡና ባንክ አ.ማ ባለአክሲዮን የሆነ/ች እና ቢመረጥ/ብትመረጥ በዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት ለመሥራት ፈቃደኛ የሆነ/ች፣
  3. ለቦታው የተገቢነት እና የብቃት መስፈርት (Fit and Proper) የሚጠይቀውን  የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ያጠናቀቀ/ች፣
  1. በቢዝነስ ማኔጅመንት፤ በባንክ ሥራ፤ በፋይናንስ፤ በአካውንቲንግ፤ በሕግ፣ በኦዲቲንግ፤ በኢኮኖሚክስ፤ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፤ በኢንቨስትመንት ማኔጅመንት የትምህርት መስክ የተመረቁና የጾታ ስብጥራቸውም ተመጣጣኝ ቢሆን ይመረጣል፣
  2. የቡና ባንክም ሆነ የሌሎች ባንኮች ተቀጣሪ ሠራተኛ ያልሆነ/ነች፤ እንዲሁም የማንኛውም የፋይናንስ ተቋም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ያልሆነ/ነች፤
  3. ተጠቋሚው የሕግ ሰውነት ያለው ድርጅት ከሆነ ድርጅቱን ወክሎ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ለመሆን የሚወዳደረው የተፈጥሮ ሰው ማንነትና የትምህርት ደረጃ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ መጥቀስ፤
  4. የቡና ባንክ አ.ማ የዳይሬክተሮች ቦርድ አስመራጭ ኮሚቴ አባል ያልሆነ/ነች፤
  5. ቡና ባንክ አክሲዮን ማህበርን ለስድስት ተከታታይ ዓመታት በቦርድ አባልነት አገልግለው ከቦርድ አባልነት የለቀቁ ከሆነ ከለቀቁበት ጊዜ ጀምሮ ስድስት ዓመታት የሆናቸው (የሞላቸው)፤
  6. በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው/ያላት እና የጸዳ የፋይናንስ አቋም ያለው/ያላት፤
  7. በሕዝብ ዘንድ መልካም ሥነምግባር፣ ማሕበራዊ ተቀባይነት ያለው/ያላት እና ሕግን በመተላለፍ በኢትዮጵያም ሆነ በውጭ አገራት በወንጀል በመከሰስ ተፈርዶበት/ባት የማያውቅ/የማታውቅ፤
  8. ለመንግሥት ባለሥልጣናት መረጃን በመከልከል፤ የተሳሳቱ የሂሳብ ወይም ሌሎች ሰነዶችን በመስጠት የተቆጣጣሪ አካላትን መመሪያዎች ባለመቀበል እና ባለመገዛት በመንግሥት ባለሥልጣናት አስተዳደራዊ የእርምት እርምጃዎች ተወስዶበት/ባት የማያውቅ/የማታውቅ፤
  9. የንግድ ሥራን ከመተግበር ወይም ድርጅትን ከመምራት አኳያ በፍርድ ቤት የመክሰር ውሳኔ ያልተላለፈበት/ባት፣ ከታክስ እና ከባንክ ክፍያዎች ጋር በተያያዘ ግዴታዎቹን/ቿን በአግባቡ የተወጣ/ች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

  ለበለጠ መረጃ በስልክ ቁጥር 011-8-722845 ወይም በ011-1-264357 በመደወል ባለአክሲዮኖች ማብራሪያ ማግኘት ይችላሉ፡፡

  ማሳሰቢያ፤

  አስመራጭ ኮሚቴው ከሐምሌ 01 ቀን 2013 ዓ.ም በፊትም ሆነ ከጥቅምት 01 ቀን 2014 ዓ.ም በኋላ የሚቀርቡ ጥቆማዎችን የማይቀበል መሆኑን ከወዲሁ ያሳስባል፡፡

  NameDownloads
  እጩ መጠቆሚያ ቅጽ

  የቡና ባንክ አ.ማ

  የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት አስመራጭ ኮሚቴ

   

  Bunna Bank