New to site?


Login

Lost password? (X)

Already have an account?


Signup

(X)
Farooq

ቡና ባንክ ቁጠባ የጀመሩ መምህራን እና የጤና ባለሞያዎችን ሸለመ

HomeNewsቡና ባንክ ቁጠባ የጀመሩ መምህራን እና የጤና ባለሞያዎችን ሸለመ
11
Oct
ቡና ባንክ ቁጠባ የጀመሩ መምህራን እና የጤና ባለሞያዎችን ሸለመ
  • Author
    Genet Fekade
  • Comments
    0 Comments
  • Category

በስድስት ወር ብቻ ከ 66ሺህ በላይ መምህራንና የጤና ባለሙያዎቸ በመርሃግብሩ ተሳታፊ ሆነዋል

(ጥቅምት 01ቀን 2014 ዓ.ም )

ቡና ባንክ ላለፉት ስድስት ወራት ባካሄደውና ከ 66 ሺህ በላይ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች በተሳተፉበት  የመጀመሪያ ዙር የመምህራን እና የጤና ባለሞያዎች “ይቆጥቡ ይሸለሙ” መርሃግብር አሸናፊ ለሆኑ ዕድለኞች ያዘጋጀውን ሽልማት በይፋዊ ስነስርዓት አስረከበ።

ሰኞ ጥቅምት 1 ቀን 2014 ዓ.ም በግዮን ሆቴል በተካሄደው የሽልማት አሰጣጥ ስነስርዓት ላይ ለዕድለኞች ሽልማት የሰጡት የቡና ባንክ ዋና ስትራቴጂ ኦፊሰር አቶ መንክር ሃይሉ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ የተሰማሩ ዜጎች ቁጠባን ባህል በማድረግ ህይወታቸውን እንዲያሻሽሉና በሃገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ባንኩ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ያደረገ የቁጠባ መርሃ ግብር ዘርግቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ከነዚህም መካከል ትውልድን በእውቀት የማነጽ እና የህዝብን ጤና የመጠበቅን ከባድ ሃላፊነት የተሸከሙ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች በአበርክቷቸው ልክ ህይወታቸው እንዲሻሻል ባንኩ የአገልግሎቶቹ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን የቁጠባ መርሃ ግብር ዘርግቶ ተግባራዊ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ቡና ባንክ ለነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት ሰጥቶ አንድም የቁጠባ ባህላቸውን እያሳደጉ የባንኩ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፣ በሌላ በኩልም በመቆጠባቸው ብቻ ተሸላሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው መርሃ ግብር በመቅረጽ የቅስቀሳ እና ግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት ሲያካሂድ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በዚህም በስድስት ወራት ብቻ ከ 66ሺህ በላይ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች በስማቸው ወደተዘጋጀው የቁጠባ መርሃ ግብር በመቀላቀል መቆጠብ መቻላቸውን ዋና ስትራቴጂ ኦፊሰሩ በንግግራቸው አስታውቀዋል።

ቡና ባንክ ይህንን ልዩ የማበረታቻ ሽልማት የታከለበት የቁጠባ መርሃ ግብር የጀመረው መምህራንና የጤና ባለሙያዎች እንደቁጠባ መጠናቸው የባንክ መርሆችን ባማከለ አሰራር ለህይወትና ኑሯቸው መሻሻል የሚያግዛቸው የባንክ አገልግሎቶች በመስጠት ማህበራዊ ሃላፊነቱን መወጣት ያለበት መሆኑን በማመን ነው ብለዋል።

በዚህ የቁጠባ እና ሽልማት መርሃግብር ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ እስከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ በመምህርነት የሚያገለግሉና  በትምህርትና ተያያዠ ደጋፊ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ዜጎች እንዲሁም በጤና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሃኪሞች፣ ነርሶች፣ ጤና ረዳቶች፣ የማህበረሰብ ጤና ባለሙያዎችና  ከህክምና ሙያ ጋር ተያያዠነት ያላቸውን የፋርማሲ ፣ የባዮሜዲካል ዕቃዎች ጥገናና ራዲዮሎጂ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ተሳታፊ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

መርሃ ግብሩ እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎቸ በቡና ባንክ ቅርንጫፎች ሂሳብ ከፍተው የዚህ የልዩ ቁጠባ አገልግሎት ተሳታፊ ሆነውና በሂሳብ ቁጥራቸው ከ ብር 400 ጀምረው ሲቆጥቡ የሽልማት ዕጣ ቁጥር የሚያገኙበት አሰራር መዘርጋቱንም ስትራቴጂ ኦፊሰሩ ጠቁመዋል።

በዚህም ለዕጣው አሸናፊዎች  ዘመናዊ 2020 ሞዴል ሱዙኪ ዲዛየር መኪናን ጨምሮ 12 ዘመናዊ ላፕቶፖች፣ 12 ታብሌቶች፣ 24 ስማርት የሞባይል ስልክ ቀፎዎች እና 6 የእረፍት ጊዜ ሽርሽር ሙሉ ወጪ የተሸፈነላቸው የታሪካዊ ቦታዎች ጉብኝት ፓኬጆች መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

ይህ የመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብር ሲጠናቀቅ በብሄራዊ ሎተሪ ኣዳራሽ ይፋዊ የእጣ ማውጣት ስነስርአት የተካሄደ መሆኑን ያስታወሱት አቶ መንክር በቁጠባ አገልግሎቱ ላይ ሲሳተፉ ከቆዩ መምህራን እና የጤና ባለሞያዎች መካከል 55 ደንበኞች የተዘጋጁት እጣዎች አሸናፊ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ይህም ባለሙያዎቹ የሙያ ግዴታቸውን በመወጣት ለህዝብ ከሚያበረክቱት ድርሻ ባሻገር ግላዊ ህይወታቸውን ለማሻሻል በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ቡና ባንክ አጋዠ ሆኖ በመምጣት የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያዳብሩና የነገ ህይወታቸውን እንዲቀይሩ የሚያበረታታቸው መሆኑን ነው ዋና ስትራቴጂ ኦፊሰሩ ያብራሩት።

ዋና ስትራቴጂ ኦፊሰሩ ንግግራቸውን ካጠቃለሉ በኋላ ለዕጣ አሸናፊዎቹ የተዘጋጁትን ሽልማቶች አስረክበዋል። የ1ኛ ዕጣ ዘመናዊ አውቶሞቢል አሸናፊ የሆኑት የቅድመ መደበኛና 1ኛ ደረጃ  ት/ቤት መምህር አቶ አስታጥቄ ወንድሙ የዚህ ሽልማት ባለዕድል መሆናቸው ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። የቁጠባ ባህላቸውን በማዳበር ወደፊት ራዕያቸውን ለማሳካት የጀመሩትን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረው ቡና ባንክ ይህንን እድል በማመቻቸቱ ምስጋና አቅርበዋል።

ከተቋቋመ 12 ዓመታት ያስቆጠረው ቡና ባንክ በመላው ሃገሪቱ 315 ቅርንጫፎች ያሉትና በየጊዜው አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት የደንበኞቹን ቁጥር ከ 1.5 ሚሊዮን በላይ ማድረስ የቻለ የግል ባንክ ሲሆን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያማከለ፣ ፍላጎትና አቅማቸውን ያገናዘበ የልዩ ቁጠባና ብድር አገልግሎቶችን በማመቻቸት ብዙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደባንክ አገልግሎት ማምጣት ችሏል።

በቅርቡ ወደ ህዝብ መጓጓዣና የጭነት ትራንስፖርት ዘርፍ አንቀሳቃሾች ቁጠባ መርሃ ግብር ያደገው የታክሲና ባጃጅ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶችና ቁጠባና ሽልማት መርሃ ግብር ከፍተኛ የደንበኞች ቁጥር ያስመዘገበበት ቀዳሚው መርሃ ግብር መሆኑ በስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

Tags:

    Bunna Bank