-
AuthorGenet Fekade
-
Comments0 Comments
-
Category

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ለተማሪዎች ምግባ ፕሮግራም ቃል የገባውን የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በዛሬው ዕለት ለከተማው አስተዳደር አስረክቧል።
በሸራተን አዲስ በተካሄደው የድጋፍ ገንዘብ ርክክብ ስነስርዓት ላይ ተገኝተው የባንኩን የ1 ሚሊዮን ብር ቼክ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያስረከቡት የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ቺፍ ኮርፖሬት ሰርቪስ ኦፊሰር አቶ ሙሉነህ አያሌው ናቸው።
በስነስርዓቱ ላይ የሁሉም ባንኮች ተወካዮች ተገኝተው ለፕሮግራሙ ቃል የገቡትን የገንዘብ ድጋፍ አስረክበዋል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚማሩ ተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም የሚውለውን የገንዘብ ድጋፍ ከፋይናንስ ተቋማቱ ከተረከቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር የከተማው አስተዳደር ያደረገውን ጥሪ በመቀበል የድጋፍ እጃቸውን ለዘረጉ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ምስጋና አቅርበዋል።
ከድጋፉ በአጠቃላይ 32.5 ሚሊዮን ብር መገኘቱን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባዋ የፋይናንስ ተቋማት አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች ለመመገብ ያደረጉት ድጋፍ የነገ የባንክ እና ኢንሹራንስ መሪዎች የሚሆኑ ህጻናትን የመደገፍ ተግባር በመሆኑ ተጠናከሮ ሊቀጥል ይገባዋል ነው ያሉት።
ቡና ኢንተርናሽናል ባንክን ጨምሮ ተቋማዊ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ቁርጠኝነታቸውን በተግባር ያሳዩ ትን ባንኮች በሙሉ ምክትል ከንቲባዋ አመስግነዋል።ለሌሎችም አርአያ ስለሆናችሁ እናመሰግናለን ነው ያሉት።
ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በቅርቡ ከዚህ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ድጋፍ በተጨማሪ ለገበታ ለሃገር የ10 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።
ጥንቅር ኮ/ኮ/ፕ/ዋና ክፍል