New to site?


Login

Lost password? (X)

Already have an account?


Signup

(X)
Farooq

ቡና ባንክ በለውጥ ልህቀት ዘርፍ ዓለምአቀፍ ሽልማት አገኘ

HomeNewsቡና ባንክ በለውጥ ልህቀት ዘርፍ ዓለምአቀፍ ሽልማት አገኘ
31
Dec
ቡና ባንክ በለውጥ ልህቀት ዘርፍ ዓለምአቀፍ ሽልማት አገኘ
  • Author
    Genet Fekade
  • Comments
    0 Comments
  • Category

ቡና ባንክ በለውጥ ልህቀት (ትራንስፎርሜሽን ኤክሰለንስ) ዘርፍ በኮር ባንኪንግ ባስመዘገበው የላቀ አፈጻጸም የ7ኛው ዙር የኢንፎሲስ ፊናክል ኢኖቬሽን አዋርድ 2021 ዓለምአቀፍ ሽልማት አሸናፊ ሆኗል።

ባንኩ አሸናፊ የሆነው በውድድሩ ተሳታፊ ከነበሩ 270 የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ በመካከለኛ ደረጃ ባንኮች መካከል በተካሄደ ውድድር ነው። በዚህ ውድድር ቡና ባንክ በኮር ባንኪንግ የላቀ አፈጻጸም የሁለተኛ ደረጃ ሽልማት አሸናፊ ሆኗል።

ውድድሩ የተካሄደው በምርት ፈጠራ፣ በአቅርቦት ፈጠራ፣ በደንበኞች አገልግሎት ማሻሻያ፣ በኮርፖሬት ባንኪንግ፣ በዲጂታላይዜሽን፣ በአካባቢ ተኮር ፈጠራ፣ በስራ ሂደት ማሻሻያ፣ በለውጥ ልህቀት፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መር ፈጠራ፣ በቢዝነስ ሞፈዴል ፈጠራ፣ እና በኮቪድ ምላሽ ፈጠራ ዘርፎች ነው።

ከመላው ዓለም የተውጣጡ 270 ያህል የባንክና ፋይናንስ ተቋማት ተወዳዳሪዎች በነበሩበትና በ10 ዘርፎች ተከፍሎ በተካሄደው በዚሁ ውድድር ላይ ቡና ባንክ በለውጥ ልህቀት ምድብ የኮር ባንኪንግ ዘርፍ የላቀ አፈጻጸም ይዞ በመቅረብ ተወዳድሯል።

በዚህ ውድድርም ባንኩ የኢንፎሲስ ፊናክል ኢኖቬሽን አዋርድ 2021 ሽልማት 2ኛ ደረጃ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል።
ባንኩ ለዚህ ውጤት የበቃው በተጠቃለለው 2021 የፈረንጆች ዓመት ዘርፍ ባስመዘገበው ለውጥ እና በተለይም በኮር ባንኪንግ አፈጻጸም ባስመዘገበው የላቀ ውጤት ተመርጦ ነው።

የዘንድሮው ተወዳዳሪዎች የተፎካከሩት በአዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችና ትግበራዎች እንዲሁም በልዩ አቀራረቦች ለተገልጋዮቻቸው አዲስ እሴት ማቅረብ መቻላቸው ተገምግሞ ሲሆን ይህንን መስፈርት ማሟላት የቻሉ ለሽልማት በቅተዋል።

ተወዳዳሪ ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት በሙሉ በ10ሩም ዘርፍ ያካሄዱትን ፉክክር በዓለም አቀፍ የባንክ ባለሙያዎችና የቴክኖሎጂ መሪዎች የተዋቀረው የዳኞች ኮሚቴ ሲመራው ቆይቷል። ኮሚቴው ተወዳዳሪዎች ያቀረቧቸውን የስራ ውጤቶች ከፈጠራ ባህሪያቸው፣ ካስገኙት ጥቅም እና ከቅለትና ክብደት አንጻር ከገመገመ እና ከመዘነ በኋላ ነጥብ ሰጥቷል።በዚህም ቡና ባንክን በመካከለኛ ባንኮች ዘርፍ በምድቡ ባሳየው አፈጻጸም የሁለተኛ ደረጃ ተሸላሚ አድርጎታል።

መቀመጫውን ህንድ ያደረገው ይህ የሽልማት ተቋም ለባንኩ ካበረከተው የዋንጫና የሰርተፍኬት ሽልማት ጨማሪም በባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ ዓለማየሁ ስም በህንድ አገር የዛፍ ችግኝ ተክሏል። የተተከለው ችግኝ ከየትኛውም ዓለም በዲጂታል ኮድ ሪደር ሊታይና የዕድገት ክትትል ሊደረግለት እንዲችል ሆኖ የተዘጋጀ መሆኑንም ተቋሙ ለባንኩ በላከው ደብዳቤ አስታውቋል።

ተሸላሚዎች ይፋ በተደረጉበት ስነስርዓት ላይ የኢንፎሲስ ፊናክል ቺፍ ቢዝነስ ኦፊሰርና ዓለምአቀፍ ሃላፊ ሳናት ራኦ (Sanat Rao) ባደረጉት የእንኳን ደስ አላችሁ ንግግር “ አሁን ያለንበት ዘመን ያልታሰቡ ለውጦች የሚገጥሙበት ፣ ተወዳዳሪነትን ለማስቀጠልም ደንበኛ ተኮር የፈጠራ ተግባር በእጅጉ የሚፈለግበት ወቅት ነው” ብለዋል።

እንደሳናት ራኦ ገለጻ ዓለምን የገጠማት የኮቪድ 10 ወረርሽኝ በሁሉም ስፍራ የሚገኙ ባንኮች አዳዲስ የቢዝነስ ሞዴሎችን በመቅረጽና የፈጠራ ስራን ተግባራዊ በማድረግ በልዩ ልዩ አቀራረብ ደንበኞቻቸውን ለማገልገል ምክንያት ሆኗቸዋል። በዚህም ተቋማዊ ብቃታቸውን በማዳበር የዲጂታል አገልግሎትን እንዲተገብሩ አድርጓቸዋል። በዚህ ውድድር የተሳተፉም ይሁን አሸናፊ የሆኑ ተቋማት በሙሉ ይህንን ፈተና ለመቋቋም ከፍ ያለ ጥረት ያደረጉና ችግሩን በድል የተወጡ ናቸው።

በመጨረሻም የዘንድሮው ሽልማት ተካፋዮች በተለይም ለውጥ ማምጣት በሚችል የባንክ አገለግሎት ቴክኖሎጂን ማዕከል ባደረገ አፈጻጸም የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የሚታትሩ መሆኑን ድርጅታችን ይገነዘባል ብለዋል ሃላፊው።ተወዳዳሪ ባንኮች በቀጣዩ ዓመትም ከዚህ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሁላችንም ምኞት ነው ብለዋል።

ቡና ባንክ በ2030 በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሶስት ከፍትኛ ባንኮች አንዱ የመሆን ራዕይ ሰንቆ ያንን ተግባራዊ ለማድረግ በትጋት እየሰራ የሚገኝ የፋይናንስ ተቋም ነው። ከ16ሺህ በላይ በሆኑ ባለአክሲዮኖች የተቋቋመው ቡና ባንክ ከተመሰረተ 12 ዓመታት የሞላው ሲሆን የዘንድሮውን የበጀት ዓመት በሁሉም የባንክ አገልግሎት ዘርፍች ከፍ ያለ ውጤት በማስመዝገብ አጠናቋል።

Tags:

    Bunna Bank