- የደጃች ውቤ ቅርንጫፍ ደንበኛ የቤት መኪና አሸናፊ ሆነዋል
ሰኔ 09 ቀን 2014 ዓ.ም
ቡና ባንክ ለመምህራን እና የጤና ባለሞያዎች ለ2ኛ ጊዜ ያዘጋጀውንና ላለፉት ወራት ሲያካሂድ የቆየውን ይቆጥቡ ሸለሙ መርሃግብር ማጠናቀቁን ምክንያት በማድረግ አሸናፊዎች ይፋ የሆኑበትን የሎተሪ ዕጣ ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም በብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ በህዝብ ፊት በይፋ አውጥቷል፡፡
የሃገር ባለውለታ የሆኑትን መምህራንና የጤና ባለሙያዎችን ለማበረታታትና የቁጠባ ባህልን ለማዳበር ታልሞ በባንኩ የተዘጋጀው የመምህራን እና የጤና ባለሞያዎች ቁጠባ በሁሉም ደረጃ ላይ የሚገኙ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎችን ተሳታፊ ያደረገ የቁጠባ መርሃ ግብር ነው፡፡
መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች ትውልድን በእውቀት የማነጽ እና የህዝብን ጤና የመጠበቅን ከባድ ሃላፊነት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚሸከሙ ምሰሶዎች መሆናቸውን ቡና ባንክ በጽኑ ያምናል ፡፡
ትምህርትና ጤና የአንድ ሃገር የዕድገት ማስቀጠያ ምሰሶዎች እንደመሆናቸው ሃገር ጤናማ ስርዓት ገንብታ ወደዕድገት የምታመራው አንድም በዕውቀት የታነጸ ፣ በሌላ በኩልም ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ሲኖራት ነው።
ቡና ባንክ የሃገር ባለውለታዎች ናቸው ብሎ የሚያምንባቸውን በእነዚህ ሁለት የሙያ ዘርፍ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች ታሳቢ የደረገውን ሁለተኛውን ዙር “የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች የቁጠባ እና ሽልማት መርሃ ግብር” ላለፉት ወራት ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል።
መርሃ ግብሩ 55 መምህራንና የጤና ባለሙያዎችን በአምስት የሽልማት ዘርፎች ከመኪና ጀምሮ ሙሉ ወጪው የተሸፈነ የሽርሽር ጉዞ ድረስ ተሸላሚ በማድረግ ለማበረታታት ያለመ ነው።
በዚህ መሰረትም በዛሬው እለት በብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ በተካሄደው የዕጣ ማውጣት ስነስርአት የደጃች ውቤ ቅርንጫፍ ደንበኛ የሆኑት አስናቀች አበበ በሎተሪ ቁጥር 4909927 የ2021 ሞዴል ሱዙኪ ዲዛየር መኪና አሸናፊ ሆነዋል፡፡
በየደረጃው ለሽልማት የተዘጋጁ 12 ላፕቶፖች፣ 12 ታብሌቶች፣ 24 ስማርት የሞባይል ስልኮች እንዲሁም 6 የእረፍት ጊዜ ሽርሽር ሙሉ ወጪ የተሸፈነላቸው የታሪካዊ ቦታዎች ጉብኝት ፓኬጆች ለእድለኞች ደርሰዋል፡፡
ባንኩ እነዚህ የሃገር ባለውለታዎች አንድም የቁጠባ ባህላቸውን እያሳደጉ የባንኩ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፣ በሌላ በኩልም በመቆጠባቸው ብቻ ተሸላሚ መሆን የሚችሉበት መርሃ ግብር ከመዘርጋት በተጨማሪ በተጠቃሚዎቹ በመበረታታት ቀጣይ ለነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሆኑ ልዩ ልዩ የባንክ አገልግሎቶችን ቀርጾ ተግባራዊ ለማድረግ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ቡና ባንክ አ.ማ ከ12 ዓመታት በፊት የተቋቋመና 339 በደረሱ ቅርንጫፎቹ በኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ የግል ባንክ ሲሆን ከ13ሺህ በላይ በሆኑ ባለአክሲዮኖች ባለቤትነት የሚተዳደር፣ በሃገሪቱ ከሚገኙ ባንኮች ውስጥ የብዙሃን ባንክ ተብሎ በመጠራት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ የግል ባንክ ነው።
ባንኩ ከ 1.9 ሚሊዮን በላይ ለደረሱ ደንበኞቹ ቀልጣፋ የባንክ አገልግሎት በመስጠትና በየጊዜው አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት በብዙ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ተዓማኒነትን ያተረፈ ባንክ ሲሆን ከሚለይባቸው ተግባራት አንዱና ዋናው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያማከለ፣ ፍላጎትና አቅማቸውን ያገናዘበ የልዩ ቁጠባና ብድር አገልግሎቶችን ማመቻቸቱ ነው።