Bunna Bank

ቡና ባንክ እና አኳ ፎር ኦል በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የ2 ሚሊዮን ዩሮ የውኃና የጤናና የንጽህና አጠባበቅ (WASH) ፋይናንሲንግ ፈንድ ስምምነት ይፋ አደረጉ

• “ባንኩ ይህንን ፈንድ በማቅረብ ለማህበረሰብ አገልግሎቶች ዕድገት ያለውን     
• ቁርጠኝነትና አርአያነቱን በተግባር አሳይቷል”  ተብሏል

ቡና ባንክና ዓለም አቀፉ አኳ ፎር ኦል (Aqua for All)  ለ WASH ዘርፍ የተሰጠ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የሁለት ሚሊዮን ዩሮ የተዘዋዋሪ ብድር አቅርቦት (Revolving Credit Facility) ስምምነት ይፋ አደረጉ።

ስምምነቱ በሂልተን አዲስ ሆቴል መስከረም 22 ቀን 2018 ዓ.ም የተፈረመ ሲሆን ከቡና ባንክ ወገን የባንኩ ቺፍ ስትራተጂና ፓርትነርሺፕ ኦፊሰር አቶ ሙሉነህ አያሌው እንዲሁም ከአኳ ፎር ኦል ወገን ደግሞ የተቋሙ የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ጋሻዬ ቸኮል ፈርመዋል፡፡

ስምምነቱ በኢትዮጵያ የውሃ፣ የንጽህና እና የጤና አጠባበቅ (WASH) አገልግሎቶችን የፋይናንስ ክፍተት በመሙላት ረገድ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ተጠቃሽ እርምጃ ሲሆን የፋይናንስ ድጋፉ ዘላቂ የWASH አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት ላይ ያተኮረ መሆኑም ተገልጿል።

የ1.5 ሚሊዮን ዩሮ የብድር አቅርቦቱ ከቡና ባንክ በተዘዋዋሪ ብድር (Revolving fund) መልክ የቀረበ ካፒታል ሲሆን ቀሪው 500,000 ዩሮ ደግሞ ከአኳ ፎር ኦል (በሆላንድ መንግሥት እና በኮንራድ ኤን. ሂልተን ፋውንዴሽን ድጋፍ) ከተገኘ የሥራ ማስጀመሪያ ካፒታል የተገኘ ነው፡፡

የቡና ባንክ ቺፍ ስትራቴጂና ፓርትነርሽፕ ኦፊሰር አቶ ሙሉነህ አያሌው በመክፈቻ ንግግራቸው “የWASH ዘርፍ ትላልቅ ፈተናዎች እንደሚገጠሙት እንረዳለን፤ በበተለይም ተደራሽነት፣ የአቅም ማነስ እና ዘላቂነት አሁንም መፍትሄ የሚሹ አስቸኳይ ችግሮች ናቸው” ብለዋል፡፡

አቶ ሙሉነህ እንዳሉት እነዚህን ፈተናዎች ለመፍታት አዳዲስ ፈጠራ የታከለባቸው መፍትሔዎች፣ ጠንካራ ትብብሮች እና ዘላቂ የፋይናንስ ሥርዓቶችን መዘርጋት አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ የስምምነቱ ፋይዳም ይህንኑ መፍትሄ ወደስራ ማስገባት ነው ብለዋል፡፡

እንደአቶ ሙሉነህ ገለጻ  ቡና ባንክ ለWASH ዘርፍ ታስቦ የተዘጋጀ ተዘዋዋሪ ብድር ያቀርባል፤ ይህ ብድር ለማይክሮፋይናንስ ተቋማት ጥቅል ብድሮችን በመስጠት በስሩ ተጠቃሚ የሚሆን እያንዳንዱ ቤተሰብ ተመጣጣኝ የውሃ፣ የንፅህና እና የጤና አገልግሎቶች እንዲያገኙ ያስችላል፣ እንዲሁም ለWASH ዘርፍ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ቀጥተኛ ብድሮችን በማቅረብ መሠረተ ልማቶችን ለማስፋትና አስፈላጊ አገልግሎቶችን ለማሻሻል ይረዳል፡፡

ቡና ባንክ ለዚሁ ዓላማ ታስቦ የተዘጋጀ ፈጠራ የታከለበት የፋይናንስ መፍትሄ በማቅረብ የኢትዮጵያን የውሃ እና የንፅህና ሁኔታ ለማሻሻል ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት አሳይቷል ነው ያሉት አቶ ሙሉነህ ።

አቶ ሙሉነህ በንግግራቸው ማጠቃለያ “ ቡና ባንክ የባንክ አገልግሎት ከመስጠት በላይ ማህበረሰቦችን ለማጠናከር፣ የሰዎችን ኑሮ ለማሻሻል እና ለዘላቂ የወደፊት ህይወት መሠረት ለመጣል የለውጥ አነሳሽ ለመሆን ይተጋል፤  ይህ ሞዴል በኢትዮጵያ ውስጥ በፋይናንስ ተቋማት እና የልማት አጋሮች መካከል ሰፊ ትብብርን እንደሚያበረታታ ተስፋ እደርጋለሁ” ብለዋል።

በስምምነቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የAqua for All የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ጋሻዬ ቸኮል  በበኩላቸው ተዘዋዋሪ የብድር አቅርቦት ኢትዮጵያ ለገጠማት የWASH ፈተናዎች መልስ የሚሰጥ መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡ “ ይህ ዘላቂ የፋይናንስ ዘዴ ባንኮችን፣ ማይክሮፋይናንስ ተቋማትን፣ ኢንተርፕራይዞችን እና የልማት አጋሮችን በአንድ ላይ በማገናኘት የፋይናንስ ክፍተቱን ለመሙላት ይረዳል” ነው ያሉት አቶ ጋሻዬ፡፡
አክለውም “ቡና ባንክ በአገሪቱ ይህን ልዩ የፋይናንስ ድጋፍ በማቅረብ በዘርፉ የመጀመሪያው የፋይናንስ ተቋም ነው፡፡ ባንኩ ይህንን ማድረጉ ለማህበረሰብ አገልግሎቶች ዕድገት ያለውን ቁርጠኝነትና መሪነቱን አጉልቶ ያሳየ አርዓያነት ያለው ተግባር ነው” ብለዋል፡፡

ይህ የብድር ፋሲሊቲ በፕሮጀክት ጊዜው ውስጥ ከ17,500 በላይ ደንበኞች እና 865 አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚ በማድረግ፣ ለኢትዮጵያ የWASH ግቦች መሳካት ቀጥተኛ እና ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

ፈንዱን በማስተዳደር ረገድ ግራንት ቶርተን (Grant Thornton) ኃላፊነቱን የወሰደ ሲሆን፣ የትግበራ አጋሮቹ ደግሞ በኢንተርፕራይዝ እና ፋይናንስ ሥነ-ምህዳር ድጋፍ ልምድ ያላቸው አይስ አዲስ (Ice Addis) እና ፌር ኤንድ ሰስቴይኔብል (Fair & Sustainable) ተቋማት መሆናቸው በስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡

በይፋዊ የማስጀመሪያ መድረኩ ላይ የተገኙ ባለድርሻ አካላት እንደገለጹት በንግድ ፋይናንስ አማካኝነት ለWASH ዘርፍ ድጋፍ በማሰባሰብ ረገድ የኢትዮጵያ ሞዴል በአፍሪካ ቀጠና ሊስፋፋ የሚገባው አሰራር ነው፡፡

በስነስርዓቱ ላይ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተጋበዙ አንግዶች፣ የአነስተኛ ብድር አቅራቢ ተቋማት ሃላፊዎች፣ የWASH እና አኳ ፎርኦል ሃላፊዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This will close in 0 seconds

You cannot copy content of this page