በቡና ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ የተመራ ልዑክ ከስራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ጋር ተወያየ
በቡና ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ የተመራ የባንኩ ከፍተኛ የስራ አመራር ልዑክ ከስራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ጋር በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
መስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም በክብርት ሚኒስትሯ ቢሮ በተካሄደው በዚሁ ውይይት ለወጣቶች የስራ ፈጠራ አቅም ግንባታ እንዲሁም የፋይናንስ አካታችነትን ማስፋት በሚቻልባቸው መንገዶችና በቴክኖሎጂ ትብብርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡
የውይይቱን መጠናቀቅ ተከትሎ ክብርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ባሰራጩት መረጃ “ከቡና ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በቅንጅት መስራት በምንችልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውጤታማ ውይይት አካሂደናል፡፡ በውይይቱ በሥራ ዕድል ፈጠራ ስነ-ምህዳሩ ላይ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተደረጉ ያሉ የተናጠል ጥረቶችን ተመልክተናል፡፡ በቀጣይም በክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድል ፈጠራ እና ሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት መስኩን ጨምሮ በጋራ በሚለዩ ስትራቴጂያዊ የትብብር መስኮች ተቀናጅቶ በመስራት ውጤቱን ለማላቅ ተግባብተናል” ብለዋል፡፡
“የቡና ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ከሚኒስቴሩ ጋር ተቀናጅቶ በመስራት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ላሳዩት ተነሳሽነትም ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ለባንካችን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የሚኒስቴሩን በሰውሰራሽ አስተውህሎት የበለጸገ የሰራተኛ ገበያ መረጃ ስርዓት (Labor market information system) በተመለከተ ክብርት ሚኒስትሯ ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የባንካችን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ በገለጻው ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዘርፉን በማዘመንና በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ በማድረግ በኩል ያከናወናቸውን ተግባራት አድንቀዋል፡፡ በተጨማሪም ክብርት ሚኒስትሯ በቢሯቸው ለርሳቸውና ለስራ አመራር ቡድኑ ላደረጉት ደማቅ አቀባበል አመስግነው በውይይቱ ወቅት ለቀረቡት ገንቢ ሃሳቦችም አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የቡና ባንክ ፕሮዳክትና ሰርቪስ ኢኖቬሽን ተጠባባቂ ቺፍ ኦፊሰር አቶ ሰዋለ ቢተው፣ የባንኩ ከወለድ ነጻ የባንክ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሃመድ ናስር እና የባንኩ ኢንተርናሽናል ባንኪንግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጠና ሀይለማርያም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡









