New to site?


Login

Lost password? (X)

Already have an account?


Signup

(X)
Farooq

ቡና ባንክ የውጭ ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ለሚመነዝሩ ዳያስፖራዎች ስጦታ አዘጋጅቻለሁ አለ

HomeNewsቡና ባንክ የውጭ ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ለሚመነዝሩ ዳያስፖራዎች ስጦታ አዘጋጅቻለሁ አለ
01
Jan
ቡና ባንክ የውጭ ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ለሚመነዝሩ ዳያስፖራዎች ስጦታ አዘጋጅቻለሁ አለ
  • Author
    Genet Fekade
  • Comments
    0 Comments
  • Category

• የላቀ አፈጻጸም ላላቸው እስከ 20 ለሚደርሱ ተገልጋዮች የደርሶ መልስ የአውሮፕላን ትኬቶች እሰጣለሁ ብሏል

ቡና ባንክ የሃገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ለመጡና ገንዘባቸውን በህጋዊ መንገድ በባንክ ለሚመነዝሩ እስከ20 ለሚደርሱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ምስጋናውን ለማቅረብ የደርሶ መልስ አውሮፕላን ትኬቶች ስጦታ ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

ባንኩ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው የዜና መግለጫ እንዳስታወቀው የጥቁር ገበያ ተጽዕኖን በመቆጣጠር የውጭ ገንዘብ ዝውውርን ህጋዊነት ማረጋገጥ ለሃገር ምጣኔ ሃብት ማደግ ታላቅ አስተዋጽዖ አለው ብሏል።

ለዚህ ደግሞ በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ቁርጠኝነትን ይጠይቃል ያለው ቡና ባንክ ኢትዮጵያ ከውጭ እየደረሰባት ያለውን ያልተገባ ተጽዕኖ ለመቃወም እና ለሃገራቸውና ለህዝባቸው ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት የተደረገላቸውን ብሄራዊ ጥሪ ተቀብለው ከያሉበት የዓለም ክፍል ወደትውልድ ሃገራቸው የገቡ ዳያስፖራዎች የዚሁ ዓላማ ተጋሪ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርቧል።

“ከውጭና ከውስጥ ፈተና የገጠማት ሃገራችን በራሷ ልጆች ትብብር አስቸጋሪውን ጊዜ ትወጣለች” ያለው ቡና ባንክ እኤአ ከጃንዋሪ 1 እስከ ጃንዋሪ 23 ድረስ በብሄራዊ ጥሪው ወደሃገር ቤት መጥተው ገንዘባቸውን በቡና ባንክ ለሚመነዝሩ ወይም የሚላክላቸውን የውጭ ገንዘብ በቡና ባንክ ለሚቀበሉ የላቀ አፈጻጸም ላላቸው እስከ 20 የሚደርሱ ደንበኞቹ ወደየትኛውም የዓለም ክፍል ሊበርሩበት የሚችሉባቸው የደርሶ መልስ የአውሮፕላን ትኬት ስጦታ ማዘጋጀቱንም በመግለጫው ይፋ አድርጓል።

በተጨማሪም በሃገራቸው ቤት መግዛት ወይም መገንባት ለሚፈልጉ የዳያስፖራ አባላት በአነስተኛ የወለድ ምጣኔ በረጅም ጊዜ የሚከፈል ብድር እንደሚያቀርብም ባንኩ አስታውቋል። ብድሩን ለማግኘት የሚጠበቅባቸው ቅድመ ሁኔታ በቡና ባንክ የዳያስፖራ አካውንት መክፈትና ገንዘብ ማስቀመጥ ብቻ ነው ብሏል።

በሃገር ቤት ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባንኩ ያመቻቻቸውን ዕድሎች እንዲጠቀሙባቸውም በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል።

እንደባንኩ መግለጫ ወደኢትዮጵያ የሚገባው የውጭ ገንዘብ ለበርካታ ዓመታት በህጋዊው የባንክ ስርዓት ውስጥ ማለፍ አለመቻሉ ያስከተለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሃገር ለዜጎቿ በምታቀርበው የመሰረተ ልማት ግንባታና በአገልግሎት መስጫ ዘርፎች መስፋፋት ላይ መስተጓጎል በመፍጠር በዜጎች ህይወት ላይ አሉታዊ ጫና አሳድሯል።

ይህንን ችግር ከመሰረቱ ለመቅረፍ እና ህጋዊ የባንክ ስርዓትን የተከተለ የውጭ ገንዘብ መላክና መቀበል ሂደት ባህል እንዲሆን ለማድረግ ቡና ባንክ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ አሰራሮችን ዘርግቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱንም በምሳሌነት አንስቷል።

የሚላክላቸውንም ሆነ በእጃቸው የሚገኘውን የውጭ ገንዘብ በቡና ባንክ ለመነዘሩ ዜጎች ባንኩ ከሚሰጠው የማበረታቻ ስጦታ ባሻገር ለዘጠኝ ጊዜ በብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር የተፈቀዱ “የይቀበሉ ይመንዝሩ ይሸለሙ “ የሽልማት መርሃ ግብሮችን በመዘርጋት በርካታ ደንበኞቹን ተጠቃሚ ሲያደርግ መቆየቱም የዚህ ጥረት አንድ አካል ነው ብሏል።

በዚህም ቡና ባንክ ለዕድለኛ ደንበኞቹ እስካሁን ዘጠኝ ዘመናዊ የቤት አውቶሞቢሎችን ጨምሮ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ልዩ ልዩ ሽልማቶችን ማበርከቱን ገልጿል። 10ኛውን ዙር ተመሳሳይ ፕሮግራምም በዚሁ ሳምንት ማስጀመሩን በመግለጽ ሁሉም ዜጎች የዚህ መርሃ ግብር ተሳታፊ በመሆን የሽልማቶቹ ተቋዳሽ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርቧል።

በመጨረሻም ባንኩ ብሄራዊ ጥሪውን ተቀብለው ወደሚወዷትና ወደምትወዳቸው ሃገራቸው የገቡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን “እንኳን ደህና መጣችሁ፣ ቆይታችሁ ያማረና የሰመረ ይሁን” በማለት መልከም ምኞቱን ገልጿል።

Tags:

    Bunna Bank