• የዕጣ አሸናፊ ደንበኞች ከዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል እስከ ሞባይል ስልክ ቀፎዎች ባለቤት የሚያደርጋቸው ዕጣ ወጥቶላቸዋል
ቡና ባንክ ጥቁር ገበያ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳደረውን ተጽዕኖ ለመከላከል በማቀድ የውጭ ገንዘብን በህጋዊ መንገድ መመንዘርን ለማበረታታት የቀረጸው “የውጭ ገንዘብ ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ” አስረኛ ዙር መርሃ ግብር በይፋ በተካሄደ የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓት ተጠናቋል።
ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም በብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ በተካሄደው የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓትም 1ኛ ዕጣ የዘመናዊ የቤት አውቶሞቢል አሸናፊው ቁጥር 0004079 መሆኑ ተረጋግጧል ።
ባንኩ ላለፉት ወራት ያካሄደው ይኸው የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ መርሃ ግብር “ በቡና ይቀበሉ፣ በቡና ይመንዝሩ፣ ከቡና ይሸለሙ” በሚል መርህ የተካሄደ ሲሆን ደንበኞች ከውጭ ሀገር ከወዳጅ ዘመዶቻቸው በተለያዩ ገንዘብ ማስተላለፊያ ድርጅቶች በኩል ገንዘብ ሲላክላቸውና በቡና ባንክ በኩል ሲቀበሉ እንዲሁም የውጭ አገር ገንዘብ በቡና ባንክ ሲመነዝሩ እድለኛ የሚሆኑበት የሎተሪ መርሃ ግብር ነው፡፡
በዚሁ የሎተሪ ዕጣ አወጣጥ ስነስርአት ወቅት አንደኛ ዕጣ የሆነውን የ2021 ሞዴል ሱዙኪ ዲዛየር መኪና ጨምሮ ዘመናዊ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች ፣ ፍሪጆች፣የውሃ ማጣሪያዎች፣ ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥኖችና ስማርት ስልኮች ለ30 ዕድለኞች ደርሰዋል፡፡
ወደሃገራችን ከሚመጣው የውጭ ገንዘብ ውስጥ አብዛኛው ከመደበኛ የባንክ አገልግሎት ይልቅ በተለያየ ምክንያት ወደጥቁር ገበያ የሚገባ በመሆኑ ሃገሪቱ በተደጋጋሚ ጊዜ ለሚገጥማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንዱ ምክንያት ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል።
የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንድ ሃገር ለሚያስፈልጋት ማናቸውም የንግድ ልውውጥ ተግባር ከፍተኛ እንቅፋት የሚፈጥር ሲሆን በዚህም ሳቢያ የሚከሰት የገቢ ንግድ መቀዛቀዝ የሸቀጦች ዋጋ መጨመርን ብቻ ሳይሆን የአስፈላጊ ግብዓቶችን እጥረት በመፍጠር የኑሮ ውድነትን ያባብሳል፣ ዜጎችም በመሰረታዊ ግብዓቶች እጥረት ለችግር እንዲጋለጡ ምክንያት ይሆናል።
የውጭ ገንዘቦች ምንዛሪና መቀበል ሂደት በባንክ ብቻ እንዲተገበርና ከጥቁር ገበያ ተጽዕኖ እንዲላቀቅ ፣ በውጤቱም ሃገርና ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል ቡና ባንክ የበኩሉን ሃላፊነት ለመወጣት በተከታታይ ዙሮች ለውጭ ገንዘብ ተቀባዮችና መንዛሪዎች የማበረታቻ ሽልማት በማዘጋጀት የዘመቻ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።
እስካሁን ባንኩ በአስር ዙር ባካሄደው “የውጭ ገንዘብ ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ” መርሃ ግብር በርካቶች በህጋዊ መንገድ የውጭ ገንዘብ እንዲመነዝሩ ከማስቻሉ ባሻገር ወደጥቁር ገበያ የሚገባውን የውጭ ገንዘብ መጠን ለመቀነስ የበኩሉን አስተዋጽዖ አበርክቷል።
ቡና ባንክ ባለፉት አስር ዙሮች ባካሄደው የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ መርሀግብር ካገኛቸው ልምዶች በመነሳት የባንኩን ደንበኞች የበለጠ ለማበረታታትና ለማትጋት አስራአንደኛ ዙር የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ መርሃግብሩን በቅርቡ ይጀምራል፡፡
አንድ ሃገር በምጣኔ ሃብት ጎልብታ ዜጎቿን ተጠቃሚ ማድረግ የምትችለው ጤናማ የገንዘብ ዝውውር ስርዓት ማስፈን ስትችል ሲሆን የገንዘብ ዝውውር ደግሞ በኢኮኖሚው ውስጥ ገንቢ ሚና እየተወጣ እንዲቀጥል ለማድረግ ባንኮች የማይተካ ድርሻ አላቸው ።
ቡና ባንክም በየጊዜው በሚያካሂደው ጥናት ብዙሃኑን ህብረተሰብ ወደባንክ ስርዓት እንዲገባ፣ በዚህም የቁጠባ ባህሉን በማሳደግ ህይወቱን እንዲያሻሽል ለማስቻል የተለያዩ አገልግሎቶችን እየቀረጸ ለጥቅም ሲያውል ቆይቷል። በዚህም ከ1.9 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን በማፍራት ወደራዕዩ ስኬት የሚያደርገውን ግስጋሴ ቀጥሏል ።
ከ13 ሺህ በላይ በሆኑ ባለአክሲዮኖች የተቋቋመው ቡና ባንክ 343 በደረሱ ቅርንጫፎቹ በመላው ኢትዮጲያ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ የግል ባንክ ነው።