(ሃምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ)
ቡና ባንክ ላለፉት ወራት ሲያካሂድ በቆየው ሁለተኛው ዙር የመምህራን እና የጤና ባለሞያዎች “ይቆጥቡ ይሸለሙ” መርሃግብር አሸናፊ ለሆኑ ዕድለኞች እና አስረኛውን ዙር “የውጭ ምንዛሬ ይቀበሉ ፣ይመንዝሩ ይሸለሙ” መርሃ ግብር ማጠናቀቂያ ምክንያት በማድረግ የሽልማት ዕጣ ለወጣላቸው ደንበኞቹ ያዘጋጃቸውን ሽልማቶች በዛሬው ዕለት አስረክቧል።
ባንኩ ሃምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም በጊዮን ሆቴል ባካሄደው በዚሁ የሽልማት አሰጣጥ ስነስርዓት ላይ የ10ኛው ዙር የውጭ ምንዛሪ የዕጣ አሸናፊዎች ለሆኑት ዕድለኞች የ2021 የቤት አውቶሞቢል፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች ፣ ማቀዝቀዣዎች፣ የውሃ ማጣሪያዎች፣ ፍላት ስክሪን ቴሌቪዠኖች እና ስማርት ስልኮችን በሽልማት ያበረከተ ሲሆን ለአሸናፊ መምህራን እና የጤና ባለሞያዎች ደግሞ ዘመናዊ 2021 ሞዴል ሱዙኪ ዲዛየር መኪናን ጨምሮ 12 ዘመናዊ ላፕቶፖች፣ 12 ታብሌቶች፣ 24 ስማርት የሞባይል ስልክ ቀፎዎች እና 6 የእረፍት ጊዜ ሽርሽር ሙሉ ወጪ የተሸፈነላቸው የታሪካዊ ቦታዎች ጉብኝት ፓኬጆችን በሽልማት አስረክቧል።
በስነስርዓቱ ላይ የባንኩ የስራ ሃላፊዎች ባደረጉት ንግግር ላይ እንደተገለጸው በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች ቁጠባን ባህል በማድረግ ህይወታቸውን እንዲያሻሽሉና በሃገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ባንኩ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ያደረገ የቁጠባ መርሃ ግብር ዘርግቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ።
ከነዚህም መካከል ትውልድን በእውቀት የማነጽ እና የህዝብን ጤና የመጠበቅን ከባድ ሃላፊነት የተሸከሙ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች በአበርክቷቸው ልክ ህይወታቸው እንዲሻሻል ባንኩ የአገልግሎቶቹ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን የቁጠባ መርሃ ግብር ዘርግቶ ተግባራዊ ማድረጉም ተጠቁሟል።
ቡና ባንክ ለነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት ሰጥቶ አንድም የቁጠባ ባህላቸውን እያሳደጉ የባንኩ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፣ በሌላ በኩልም በመቆጠባቸው ብቻ ተሸላሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው መርሃ ግብር በመቅረጽ የቅስቀሳ እና ግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት ሲያካሂድ ቆይቷል።
ቡና ባንክ ይህንን ልዩ የማበረታቻ ሽልማት የታከለበት የቁጠባ መርሃ ግብር የጀመረው መምህራንና የጤና ባለሙያዎች እንደቁጠባ መጠናቸው የባንክ መርሆችን ባማከለ አሰራር ለህይወትና ኑሯቸው መሻሻል የሚያግዛቸው የባንክ አገልግሎቶች በመስጠት ማህበራዊ ሃላፊነቱን መወጣት ያለበት መሆኑን በማመን ነው ብለዋል።
በዚህ የቁጠባ እና ሽልማት መርሃግብር ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ እስከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ በመምህርነት የሚያገለግሉና በትምህርትና ተያያዠ ደጋፊ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ዜጎች እንዲሁም በጤና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ሃኪሞች፣ ነርሶች፣ ጤና ረዳቶች፣ የማህበረሰብ ጤና ባለሙያዎችና ከህክምና ሙያ ጋር ተያያዠነት ያላቸውን የፋርማሲ ፣ የባዮሜዲካል ዕቃዎች ጥገናና ራዲዮሎጂ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ተሳታፊ መሆን ችለዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪም ቡና ባንክ ቁጠባን ከማበረታታት ባሻገር ደንበኞች ከውጭ የሚላክላቸውንም ሆነ በእጃቸው የሚገኝ የውጭ ገንዘብ በቡና ባንክ ቅርንጫፎች በኩል ሲቀበሉና ሲመነዝሩ ተሸላሚ የሚያደርጋቸውን የዕጣ ኩፖን የሚቀበሉበት አሰራር በመዘርጋት ባለፉት ዓመታት ባካሄዳቸው አስር ዙሮች በርካታ ቁጥር ላላቸው ደንበኞቹ ከፍተኛ የዋጋ ግምት ያላቸውን ሽልማቶች ሲያበረክት ቆይቷል።
አሁን በተጠናቀቀወ 10ኛው ዙር “የውጭ ምንዛሪ ይቀበሉ ፣ይመንዝሩ፣ይሸለሙ” መርሃ ግብርም በተመሳሳይ በህጋዊ መንገድ የሚካሄድ የውጭ ምንዛሪ ለውጥን በማበረታታት ሃገሪቱ ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም በማረጋገጥ ረገድ ባንኩ በዘረጋው መርሃ ግብር ላይ ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦችም ተሸላሚ ሆነዋል።
ቡና ባንክ በህጋዊ መንገድ የሚመነዘር የውጭ ገንዘብ ለሃገር ብልጽግና እና ለእያንዳንዱ ዜጋ እድገት የራሱ አስትዋጽዖ ያለው በመሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ይህንን እንዲያበረታታም አሳስቧል።
በተጨማሪም ወደሃገር ቤት መምጣት ያልቻሉት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትየጵያውያን ለወዳጅ ዘመድ የሚልኩትን ገንዘብ በህጋዊ መንገድ በባንክ በማስተላለፍ ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል።
ባንኩ ከብሄራዊ ሎተሪ ባገኘው ፍቃድ 11ኛውን ዙር የውጭ ምንዛሪ ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ መርሃ ግብር እንዲሁም 3ኛውን ዙር የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች የይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ ግብር በቅርቡ በይፋ እንደሚጀምርም በስነስርዓቱ ላይ አስታውቋል።
ከተመሰረተ 12ኛ ዓመቱን በማገባደድ ላይ ያለው ቡና ባንክ በአዲስ አበባና በመላው ኢትዮጵያ በከፈታቸው 362 ቅርንጫፎቹ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ የግል ባንክ ነው።