New to site?


Login

Lost password? (X)

Already have an account?


Signup

(X)
Farooq

ብሔራዊ ባንክ የአዲሱን የቡና ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመት አፀደቀ

HomeNewsብሔራዊ ባንክ የአዲሱን የቡና ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመት አፀደቀ
20
Sep
ብሔራዊ ባንክ የአዲሱን የቡና ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመት አፀደቀ
 • Author
  admin
 • Comments
  0 Comments
 • Category
ብሔራዊ ባንክ የአዲሱን የቡና ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመት አፀደቀ
ባለፈው ሳምንት ዕውቅና የተሰጣቸው የቀድሞ የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጭንቅል

ብሔራዊ ባንክ የአዲሱን የቡና ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመት አፀደቀ

ብሔራዊ ባንክ የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ ዓለማየሁ የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲያገለግሉ ከቦርዱ የቀረበለትን ጥያቄ በማየት ሹመታቸውን ማፅደቁ ተገለጸ፡፡

ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው አቶ ሙሉጌታ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲያገለግሉ በቦርዱ ታጭተው የብሔራዊ ባንክን ውሳኔ ሲጠባበቁ ነበር፡፡

ብሔራዊ ባንክ የአቶ ሙሉጌታ ሹመት ከማፅደቁ በፊት ከመስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት መሰየማቸው አይዘነጋም፡፡

አቶ ሙሉጌታ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ታደሰ ጭንቅልን ተክተው ነው፡፡ የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ አቶ ሙሉጌታን ሲሾም፣ አቶ ታደሰ ደግሞ የባንኩ አማካሪ እንዲሆኑ ሰይሟቸዋል፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው አቶ ታደሰ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ዕውቅና ከተሰጣቸው ሦስት የባንክ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ አዲሱ የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ19 ዓመታት ያገለገሉ ናቸው፡፡ እንደ ባንኩ መረጃ አቶ ሙሉጌታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሠርተዋል፡፡ በተለይ ወደ ቡና ባንክ ከመምጣታቸው በፊት በቺፍ ቢዝነስ ኦፊሰርነትአጠቃላይ የባንኩን እንቅስቃሴ በመምራት ስትራቴጂውን በመቅረጽ፣ ዘመናዊ የሥራ ሒደቶችን  በመንደፍ፣ ፖሊሲና መመርያዎችን በማዘጋጀት የባንኩን ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ ስኬታማ እንዲሆን አድርገዋል፡፡

ቀደም ሲልም በምክትል ፕሬዚዳንትነት የደንበኞች አካውንትና ትራንዛክሽን አገልግሎት ላይ የሠሩ ሲሆን፣ በምክትል ፕሬዚዳንት የፋይናንስ ዘርፉንም እንደመሩ የሥራ ልምዳቸው ያሳያል፡፡

አቶ ሙሉጌታ የባንኩ ቺፍ ሪስክና ኮምፖሊያንስ ኦፊሰር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአካውንት አናሊሲሲ በሥራ አስኪያጅነት፣ በብድር ኦዲት ቡድን መሪነት፣ በብድር ሞኒተሪንግ ኦፊሰርነት የሥራ ልምድ እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በቦርድ አመራርነትም በርካታ ድርጅቶችን እንደመሩ የሚያመለክተው የአቶ ሙሉጌታን የሥራ ልምድ የሚያሳየው መረጃ፣ የኮሜርሽያል ኖሚኒስ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ማገልገላቸው በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ የሲዳ ቴክስታይል ቦርድ ሰብሳቢ፣ የኢትዮጵያ ህዳሴ፣ የኢትዮጵያ ኮሞዲቲ ኤክስቼንጅና ሌሎችንም ድርጅቶች በቦርድ አመራርነት ማገልገላቸው የሥራ ልምዳቸው ያስረዳል፡፡

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በኢንዱስትሪው ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ የግል ባንኮች አንዱ ነው፡፡ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀለ ዘጠኝ ዓመታት የቆየ ሲሆን፣ከባንኩ ምሥረታ ማግሥት የመጀመርያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ሲመሩ የቆዩት አቶ ነገደ አበበ ናቸው፡፡ ከዚያም በመቀጠል አቶ እሸቱ ፋንታዬና ሦስተኛው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጭንቅል ሲሆኑ፣  አቶ ሙሉጌታ አራተኛው ዋና ሥራ አስፈጻሚ  ናቸው፡፡

ቡና ባንክ ከ175 በላይ ቅርንጫፎችን በመላ አገሪቱ የከፈተ ሲሆን፣ የባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ13 ሺሕ በላይና የካፒታል መጠኑም ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይመድረሱን ከባንኩ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽንና ፕሮሞሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Tags:

  

  ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ የ11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እና 4ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ
  

  በኢትዮጵያ ንግድ ሕግ አንቀጽ 418፣ 419 እና 423 እንዲሁም በባንኩ መመስረቻ ጽሁፍ አንቀጽ 11.3.7 እና በመተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 6.3 መሠረት የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ የባለአክሲዮኖች 11ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እና 4ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ታህሳስ 11 ቀን 2013 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ ጦርሃይሎች አካባቢ በሚገኘው ጎልፍ ክለብ ውስጥ ይካሄዳል፡፡

  ስለሆነም የባንኩ ባለአክሲዮኖች በአካል ወይም በሕጋዊ ተወካዮቻችሁ አማካኝነት በተጠቀሰው ቀን፣ ሰዓትና ቦታ ጉባኤው ላይ እንድትገኙ ባንኩ በአክብሮት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

  የ4ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ አጀንዳዎች

  1) ረቂቅ አጀንዳዎችን ማጽደቅ፣

  2) በባንኩ የመመስረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ላይ ተወያይቶ ማጽደቅ

  3) የጉባኤውን ቃለ-ጉባኤ ማጽደቅ

  የ11ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ አጀንዳዎች

  1) ረቂቅ አጀንዳዎችን ማጽደቅ፣

  2) በባንኩ ውስጥ የተደረጉ የአክሲዮን ዝውውሮችን እና የአዲስ አክሲዮኖችን ሽያጭ መርምሮ ማጽደቅ፣

  3) እ.ኤ.አ የ2019/20 የዳይሬክተሮች ቦርድ ዓመታዊ ሪፖርት ማዳመጥ፣

  4) እ.ኤ.አ የ2019/20 የውጭ ኦዲተሮች ቦርድ ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርትን ማዳመጥ፣

  5) በተራ ቁጥር 3 እና 4 የቀረቡትን ሪፖርቶች ተወያይቶ ማጽደቅ፣

  6) የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጥቆማ እና ምርጫ አፈፃፀም የአሰራር ደንብ ማሻሻያን መርምሮ ማጸደቅና የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት አበልን መወሰን፣

  7) የዳይሬክተሮች ቦርድ አስመራጭ ኮሚቴን መምረጥ፣

  8) እ.ኤ.አ የ2020/21 በጀት ዓመት የዳይሬክተሮች ቦርድ ወርሃዊ አበልና ዓመታዊ ክፍያ ላይ ተወያይቶ መወሰን፣

  9) እ.ኤ.አ የ2020/21 በጀት ዓመት የውጭ ኦዲተሮችን ሹመት ማጽደቅና አበል መወሰን፣

  10) በዘመኑ የተጣራ ትርፍ አደላደል እና አከፋፈል ላይ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ መወሰን፣

  11) የጉባኤውን ቃለ-ጉባኤ ማጽደቅ፣ የሚሉት ናቸው፡፡

  ማሳሰቢያ

  1. በጉባኤው ላይ በአካል መገኘት የማይችሉ ባለአክሲዮኖች አግባብነት ካለውና ሕጋዊ ውክልና መስጠት ከሚችል የመንግሥት አካል የተሰጠ’ በስብሰባው ላይ ለመገኘትና ድምጽ ለመስጠት የሚያስችል የውክልና ሰነድ ወይም ከስብሰባው ሶስት ቀን ቀደም ብሎ ቦሌ መንገድ ከወሎ ሰፈር አደባባይ ቀጥሎ ርዋንዳ መታጠፊያ ከመድረሱ በፊት በሚገኘው የባንኩ ዋና መ/ቤት 4ኛ ፎቅ የባንኩ ፋይናንስ ዳይሬክቶሬት ቢሮ ድርስ በመቅረብ የውክልና ፎርም (ቅጽ) በመሙላት፣ ሌላ ሰው በመወከል የውክልና ሰነዱን ወይም ቅጹን ዋናውንና አንድ ቅጂ ይዘው በመምጣት በጉባዔው መሳተፍ የሚችሉ መሆኑን በአክብሮት እናስታውቃለን፡፡

  2. ባለአክስዮኖችም ሆኑ ህጋዊ ወኪሎቻቸው ወደ ስብሰባው ቦታ ሲመጡ የራሳቸውንም ሆነ የተወካዮቻቸውን ሕጋዊ የታደሰ መታወቂያ ካርድ ዋናውን እና ፎቶ ኮፒውን መያዝ አለባቸው፡፡

  3. ባንኩ የባለአክሲዮኖችን የመለያ ቁጥር ባስመዘገባችሁት ተንቀሳቃሽ ስልክ የሚልክ ሲሆን& ይህንኑ ቁጥር በስብሰባው ዕለት ይዛችሁ እንድትመጡ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡

  4. ከላይ በተ.ቁ. 2 ላይ የተገለፀውን የወካዩን ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሚያረጋግጥ ሕጋዊና የታደሰ መታወቂያ፣ ፓስፖርት ወይም መንጃ ፈቃድ ኮፒ ይዘው የማይመጡ ተወካዮች በጉባኤው ላይ መሳተፍ የማይችሉ መሆኑን በአክብሮት እናሳውቃለን፡፡ በተጨማሪም የድርጅት ተወካዮች ድርጅቱን ወክለው በስብሰባው እንዲገኙና ድምጽ እንዲሰጡ መወከላቸውን የሚያረጋግጥ የተመዘገበ ቃለ-ጉባዔ ወይም በውል አዋዋይ ፊት የተሰጠ ውክልና ዋናውን እና ኮፒውን ይዘው መቅረብ ያለባቸው መሆኑን እናስታውቃለን፣፡

  5. የብሄራዊ ባንክ ያስቀመጠውን የውክልና አሰጣጥ መጠን ገደብ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለጊዜው ያነሳ በመሆኑ ወረርሽኙን ለመከላከል ሲባል ባለአክሲዮኖች በጉባዔው በውክልና እንዲሳተፉ ይበረታታሉ፡፡

  6. ተጨማሪ መረጃ ቦሌ መንገድ ከወሎ ሰፈር አደባባይ ቀጥሎ ወደሩዋንዳ መታጠፊያ ከመድረሱ በፊት በሚገኘው የባንኩ ዋና መ/ቤት በአካል በመቅረብ ወይም በስልክ 0111580880 / 262822 / 262810 በመደወል ማግኘት ይችላሉ፡፡

  የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ

  የዳይሬክተሮች ቦርድ

  ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ

  የባለራዕዮች ባንክ!!!

  Bunna Bank