አዲስ አበባ: – ታህሳስ 12, 2017 – ቡና ባንክ እና ካቻ ዲጂታል ፋይናንሻል ሰርቪስ የቅድመ ደሞዝ ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ “አቦል ደሞዜ” የተሰኘ የዲጂታል ብድር እና ቁጠባ አገልግሎት በዛሬው እለት በይፋ አስጀምረዋል ።
ለተቀጣሪ ደመወዝተኛ የህብረተሰብ ክፍል አገልግሎት እንዲሰጥ የተነደፈው “አቦል ደሞዜ” ለሰራተኞች የደሞዝ መደረሻ የገንዘብ ፍላጎትን ለማርካት የተዘጋጀ የቅድመ ደመወዝ ብድር አገልግሎት ሲሆን ሰራተኞች ከክፍያ ቀናቸው በፊት በሚገጥማቸው የገንዘብ እጥረት ወቅት የወር ደሞዛቸውን የተወሰነ ክፍል ያለምንም ማስያዣ በብድር እንዲያገኙ የሚያስችል የፋይናንሺያል አገልግሎት ነው።




በዚህ አዲስ አገልግሎት ተጠቃሚዎች የደመወዛቸውን 33% ወይም 50% በቀላሉ ካሉበት ሆነው በካቻ የሞባይል አፕሊኬሽን ማግኘት ሲችሉ ምቹ በሆነ የአከፋፈል ዘዴ በተቀመጠው ቀነ ገደብ መሰረት ብድራቸውን መክፈል የሚችሉበት አማራጭም ተቀምጦላቸዋል ።
ሰራተኞች አገልግሎቱን ለማግኘት የቡና ባንክ ወይም የካቻ ደንበኞች መሆን እንደሚጠበቅባቸው የቡና ባንክ ቺፍ ባንኪንግ ኦፊሰር አቶ መንክር ሀይሉ ሲገልፁ “’አቦል ደሞዜ የደንበኞቻችንን ተለዋዋጭ ፍላጎት የሚያሟሉ አዳዲስ እና ተደራሽ የሆኑ የፋይናንስ መፍትሄዎችን ለማቅረብ ያለንን ቁርጠኝነት ያንፀባርቃል” ነው ያሉት ።
አገልግሎቱን ያበለፀገው የካቻ ዲጂታል ፋይናንሻል ሰርቪስ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብርሀም ጥላሁን በበኩላቸው “ካቻ በተለመደው የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ያልነበረውን ሰፊ የህብረተሰብ ክፍል ለማገልገል የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን እንደ አማራጭ ይዞ የመጣ ኩባንያ መሆኑን ገልጸው ከቡና ባንክ ጋር በመቀናጀት ይህንን የደሞዝ መዳረሻ ብድር አገልግሎትን ሲያቀርብ ታላቅ ኩራት እየተሰማው ነው ” ብለዋል ።
ቡና ባንክ እና ካቻ ዲጂታል ፋይናንሺያል ሰርቪስ የባንክ አገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነት የሚያሰፉ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለማበልፀግና ለማገልገል ዘላቂ አጋርነት የፈጠሩ ኩባንያዎች ሲሆኑ “አቦል ደሞዜ” ከዚህ ትብብር የተወለደ የመጀመሪያው አገልግሎት መሆኑም በማስጀመሪያ መርሀግብሩ ላይ ተገልጿል ።
ከተመሰረተ 15 ዓመታት ያስቆጠረው ቡና ባንክ በባንክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ላለፉት 15 ዓመታት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝና ከ4 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ያፈራ የፋይናንስ ተቋም ሲሆን በአጋርነት አገልግሎቱን ያበለፀገው ካቻ ዲጂታል ፋይናንሺያል ሰርቪስ አ.ማ ደግሞ የብሔራዊ ክፍያ ስርዓትን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 718/2003 እና የክፍያ መፈፀሚያ ሰነድ አውጪዎችን ለማስተዳደር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወጣው መመሪያ ቁጥር ONPS/01/2020 መሰረት የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ የክፍያ ሰነዶችን ለማውጣት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቁጥር NPS/PII/002/2022 ፈቃድ ያገኘ የመጀመሪያው የግል የክፍያ ሰነድ አውጪ በመሆን አገልግሎቱን ማቅረብ ከጀመረ ሁለት አመት ተኩል አስቆጥሯል።





















