(መጋቢት 7 ቀን 2014 ዓ.ም – አዲስ አበባ)
ቡና ባንክ የሚጠቀምበትን አዲስ ብራንድ አርማና ቀለም ይፋ አደረገ።
ከአንድ ዓመት በፊት “ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ” የሚለውን ስያሜ “ቡና ባንክ” ወደሚል መጠሪያ የቀየረውና በአዲስ መለያ አርማ እና ቀለም ለመምጣት የጥናትና የዝግጅት ስራዎችን ሲያከናውን የቆየው ቡና ባንክ በመጨረሻ የቀረጸውን አዲስ የብራንድ አርማና ቀለም ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርጓል።
በጋዜጣዊ መግለጫው እንደተነገረው በኢትዮጵያ ዐዕምሮአዊ ንብረት ፅህፈት ቤት ተመዝግቦ የጸደቀው አዲሱ የቡና ባንክ አርማና ቀለም ባንኩ ከምስረታው ጀምሮ ሲጠቀምበት የቆየውን አርማና ቀለም ተክቶ ስራ ላይ ውሏል።
ባንኩ ረቡዕ መጋቢት 7 ቀን 2014 ዓ.ም በኢንተርሌግዠሪ ሆቴል ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ የአርማውና መለያ ቀለሙን ትርጉም ጨምሮ አዲስ ብራንድ ማዘጋጀት ያስፈለገበት ምክንያት ተብራርቷል።
በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተብራራው አዲሱ የብራንድ አርማና ቀለም የባንኩን ራዕይ፣ ተልዕኮ እና እሴቶች እንዲወክል ሆኖ የተዘጋጀ ሲሆን ለማንኛውም አጠቃቀም ምቹ፣ በህብረተሰቡ ዘንድም በቀላሉ መታወስ እንዲችል ተደርጎ የተቀረጸ ነው።
እንደጋዜጣዊ መግለጫው ቡና ባንክ ከባለአክሲዮኖቹ፣ ከደንበኞቹ፣ ከሰራተኞቹ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት በሰበሰበው አስተያየት ላይ ተመስርቶ ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት ከዚህ ቀደም ሲጠቀምበት የቆየው መለያ ምልክት በቀላሉ ለመታወስ አስቸጋሪ እና ለመረዳትም ውስብስብ ሆኖ ቆይቷል።
የጥናቱን ውጤት መሰረት በማድረግም ለአጠቃቀም ቀላል ፣ ለመረዳት ግልጽ የሆነ እና በቀላሉ መታወስ የሚችል ፣ ከባንኩ ራዕይ፣ ተልዕኮ እና ዋና ዋና እሴቶች ጋር የተዋደደ ትርጉም መስጠት የሚችል የብራንድ አርማና ቀለም እንዲዘጋጅ መወሰኑ ተብራርቷል።
በዚህ መሰረት ባንኩ ግልጽ ጨረታ በማውጣት የብራንዲንግ ኩባንያዎችን ማወዳደሩንና አሸናፊ ከሆነው ቤሪ አድቨርታይዚንግ ከተባለ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈራርሞ ስራውን መጀመሩን ገልጿል። ኩባንያው የብራንድ አርማና ቀለም ዝግጅቱን ከብራንድ መመሪያው ሰነዱ ጋር አጠናቅቆ ለባንኩ ማስረከቡም በመግለጫው ተመልክቷል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ይፋ እንደተደረገው አዲሱ የቡና ባንክ ብራንድ አርማና መለያ ቀለም ትርጉም የሚከለተውን ይመስላል።
የብራንድ አርማ
አዲሱ የቡና ባንክ ብራንድ አርማ ከሶስት ምስሎች የተዋቀረ ነው። እነዚህም ምስሎች ዐይን፣ አድማስ እና ክብ ቅርጽ ናቸው።
- ዐይን
የሎጎው የታችኛው ክፍል የዓይን ቅርጽ አለው። ይህም መንቃትን ይወክላል።መንቃት በአዲስ መንፈስና ጉልበት የመነሳት የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው። ትጋት እና አዲስ ለውጥ ለማየት መዘጋጀት የመንቃት መገለጫዎች ናቸው።
ይህም የቡና ባንክን በአዲስ መንፈስና ጉልበት ለለውጥ መነሳት ይወክላል።
- አድማስ
የሎጎው መካከለኛ ክፍል የአድማስ ቅርጽ አለው። አድማስ የአዲስ ቀን ጅማሮና የብሩህ ተስፋ መገለጫ ነው። በሩቅ የሚታይ ፣ እንደራዕይ መዳረሻነት የሚቆጠር ምልክትም ነው።
ይህም የቡና ባንክን ባለራዕይነት የሚገልጽ ሲሆን የስኬት መዳረሻውን በአዲስ ጅማሮ፣ በብሩህ ተስፋና በጠንካራ መንፈስ ተልሞ መነሳቱንም ይወክላል።
- ክብ ቅርጽ
የሎጎው ሙሉ ቅርጽ ክብ ነው። ክብ ቅርጽ ብዙ ሆነን እንደአንድ የምንሰባሰብበት፣ የምንመክርበት፣ የምንረዳዳበት፣ ክፉና ደግን የምንካፈልበት ፣ ከትውልድ ትውልድ የተቀባበልነውን ትውፊት፣ ባህል እና ልማዳችንን የሚወክል ምልክት ነው።
ይህም ቡና ባንክ ልክ እንደቡና ስርዓታችን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በአንድ ዓላማ ጥላ ስር ያሰባሰበ ባንክ መሆኑን፣በዚህ መሰባሰብ ውስጥም ለእድገት ፣ለብልጽግና እና ለእኩል ተጠቃሚነት በአንድነት በጋራ መቆሙን ይወክላል።
የብራንድ ቀለማት
አዲሱ የቡና ባንክ ብራንድ መሰረታዊ ቀለማት ሁለት ሲሆኑ እነርሱም ‘ማሩን ሬድ’ እና ‘ኮርፖሬት ብሉ’ ናቸው።
እነዚህ ቀለማት የቀይ እና የሰማያዊ ቀለማት ንዑሳን ዘሮች ሲሆኑ ቡና ባንክን የሚገልጹ የብራንድ መለያዎች እንዲሆኑ በጥናት የተመረጡ ናቸው። ለቡና ባንክ አርማም ይሁን ለብራንድ መለያ እንዲሆኑ የተመረጡት ሁለቱ ቀለማት እንደአገባባቸው በስብጥርና በተናጥል ጥቅም ላይ ይውላሉ። የቀለማቱ ትርጉምም የሚከተለውን ይመስላል
- ማሩን ሬድ (የቀይ ቀለም ዘር) የዓላማ ጥንካሬን፣ ጥልቅ የማገልገል ፍላጎትን፣ ለስራ መነሳሳትን የሚወክል ሲሆን
- ኮርፖሬት ብሉ ( የሰማያዊ ቀለም ዘር) የምንጊዜም ታማኝነትን ፣ ለዓላማ ቁርጠኝነትን እና በእውቀት መስራትን ይወክላል
የቡና ባንክ ብራንድ ከነዚህ ሁለት መሰረታዊ ቀለማቱ (primary colors) ባሻገር ለተለያዩ የማስተዋወቂያ አገልግሎቶች በተተኪነት የሚጠቀምባቸው 42 ዝርያ ያላቸው ሰባት ተለዋጭ ቀለማት (secondary colors) አሉት።
እነዚህ ቀለማት የተቀዱት ከቡና ፍሬ የህይወት ዑደት ሲሆን ቡና ማፍራት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ደርሶ እስከሚለቀምበት ወቅት ድረስ በየጊዜው የሚኖሩትን ተለዋዋጭ ቀለማት የሚወክሉ ናቸው።
ከተመሰረተ 12 ዓመታትን ያስቆጠረውና ከ 1.8 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ማፍራት የቻለው ቡና ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንደስትሪ ዘርፍ የራሳቸውን አሻራ በማሳረፍ በስኬት ጎዳና እየተጓዙ ከሚገኙ ግንባር ቀደም የግል ባንኮች አንዱ ነው።