New to site?


Login

Lost password? (X)

Already have an account?


Signup

(X)
Farooq

ዜና መግለጫ (News release)

HomeNewsዜና መግለጫ (News release)
23
Aug
ዜና መግለጫ (News release)
 • Author
  Genet Fekade
 • Comments
  0 Comments
 • Category

ቡና ባንክ በጭነትና በህዝብ ማመላለሻ መንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ የህብረተሰብ  ክፍሎች ያዘጋጀውን አዲስ የቁጠባና ሽልማት መርሃ ግብር በይፋ ጀመረ

 • መርሃግብሩ በፈሳሽና ደረቅ ጭነቶች ማመላለሻ እንዲሁም በአነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ የህዝብ መንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለንብረቶችን፣ አሽከርካሪዎችንና  ረዳቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

(አዲስ አበባ ነሃሴ 14 ቀን 2013ዓ.ም)

ቡና ባንክ ባለፉት አመታት የመደበኛ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ባለቤቶችንና  አሽከርካሪዎችን ታሳቢ አድርጎ ለአምስት ዙሮች ሲያካሂድ የቆየውን የይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ ግብር በማስፋት በጭነትና ህዝብ ማመላለሻ መንገድ ትራንስፖርት የስራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በሙሉ ያካተተ አዲስ የ ቁጠባ እና ሽልማት  መርሃ ግብር ይፋ አደረገ።

መርሃ ግብሩ ከነሃሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ህዳር 8 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ሲሆን በማንኛውም ቀላልና ከባድ የፈሳሽ እና ደረቅ ጭነት ተሽከርካሪ፣ መደበኛ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ሚኒባሶች፣ ሚድ ባሶች፣ ሜትር ታክሲዎች፣ ባለሶስት እግር ታክሲዎች እንዲሁም የመካከለኛ እና ከፍተኛ ሃገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች  ላይ የተሰማሩ ባለንብረቶች፣ አሽከርካሪዎች  ረዳቶች እና ትኬት ቆራጮችን ተጠቃሚ ያደርጋል።

በቁጠባ አገልግሎቱ ላይ የሚሳተፉ አካላት ከሰኞ እስከቅዳሜ በየቀኑ 150 ብር ወይም በአንድ ጊዜ 900 ብር ሲቆጥቡ ወዲያውኑ አንድ ለዕልማት ብቁ የሚያደርጋቸው የሎተሪ ዕጣ ቁጥር እንዲደርሳቸው የሚደረግ ሲሆን  የቆጣቢዎቹ የቁጠባ መጠን በየ 900 ብር ልዩነት ባደገ ቁጥርም ዕድለኛ የሚያደርጋቸው የዕጣ ቁጥሮች መጠን በዚያው ልክ የሚያድግ ይሆናል።

ባንኩ ለሶስት ወራት የሚያካሂደው ይኸው ይቆጥቡ ይሸለሙ ፕሮግራም ሲጠናቀቅ ያዘጋጃቸውን ሽልማቶች በብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ድርጅት ውስጥ  በይፋዊ ስነስርዓት ዕጣ በማውጣት አሸናፊዎቹን የሚያሳውቅ ሲሆን በደማቅ ስነስርዓትም ዕጣውን ለባለዕድሎች ያስተላልፋል።

ከሶስት ወር በኋላ በብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ በይፋ በሚካሄደው የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓት ላይም የዚህ መርሃ ግብር አሸናፊ ለሆኑ ግለሰቦች በሽልማት የሚበረከቱ ሁለት የ2020 ዘመናዊ የቤት አውቶሞቢሎች፣ ሁለት ባለሶስት እግር ተሽካርካሪዎች፣ አምስት የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች፣ አምስት ዘመናዊ ማቀዝቀዣዎች፣ አምስት 55 ኢንች ቴሌቪዠኖች፣ አምስት የውሃ ማጣሪያዎች እና አስር ስማርት የሞባይል ስልኮች ተዘጋጅተዋል።

ቡና ባንክ ከግለሰቦች ህይወት ማሻሻል ባሻገር ለሃገር ኢኮኖሚ ግንባታ መሰረታዊ ሚና እንደሚጫወት የሚታመነው ቁጠባ በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል እንዲሆን ለማስቻል በየጊዜው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ የሚያደርጉ አዳዲስ የቁጠባ ፕሮግራሞችን ከማበረታቻ ሽልማቶች ጋር በመዘርጋት ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የማህበረሰብ ክፍል የባንክ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

በተለይም በዕለት ገቢ ላይ የተመሰረተ የታክሲ አገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አሽከርካሪና ባለንብረቶችን ታላሚ ባደረገውና ለአምስት ዙር ሲካሄድ በቆየው የቁጠባ መርሃ ግብር ተሳታፊ የነበሩ በርካቶች  በቆጠቡት ገንዘብ ህይወታቸውን ከማሻሻላቸው ባሻገር ቡና ባንክ ለዘርፉ ማበረታቻነት ባዘጋጃቸው አውቶሞቢሎችን ያካተቱ ሽልማቶችን በማሸነፍም በከፍትኛ ደረጃ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

አሁን አዲስ የተጀመረው የትራንስፖርት ዘርፍ የቁጠባ እና ሽልማት መርሃ ግብር ከዚህ ተሞክሮ በመነሳት የተቀረጸ ሲሆን የዘርፉ ተዋንያን ቁጠባን ባህል በማድረግ የነገ ህይወታቸውን በጠንካራ መሰረት ላይ እየገነቡ ለሽልማት እንዲበቁ የሚያግዝ ነው።

የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው የሚባለው የትራንስፖርት ዘርፍ የመሠረተ ልማት አውታሮችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቀም እንደመሆኑ የሃገራችን ምጣኔ ሃብት እጅግ አስፈላጊ አካል ከመሆኑ ባሻገር የልማትና ዕድገት ማሳለጫ አይነተኛ መሣሪያም ጭምር ነው። የትራንስፖርት መሠረተ ልማት መስፋፋት ከከፍተኛ የእድገት ደረጃዎች ጋር የተቆራነ እንደመሆኑ የትራንስፖርት ሥርዓቶች ቀልጣፋ ሲሆኑ ለተሻለ የገበያ ተደራሽነት ፣ ለበርካታ የሥራ ስምሪት እና እንደተጨማሪ ኢንቨስትመንቶች ላሉ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዕድሎች እና ጥቅሞች በር ይከፍታል።

ቡና ባንክ ለነዚህ ትልቅ ኢኮኖሚያዊና ማህበራ ሚና ለሚጫወቱ የማህበረሰብ ክፍሎች ትኩረት በመስጠት ባዘጋጀው በዚህ የቁጠባ እና ሽልማት መርሃ ግብር አንድም የቁጠባ ባህልን በማሳደግ ዜጎች የባንክ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲያግዝ  በሌላ በኩልም የዘርፉ ተዋንያን ገንዘባቸውን በመቆጠባቸው ብቻ የሚበረታቱበትን ለተሸላሚነት የሚያበቃቸውን  መርሃ ግብር በመዘርጋት አጋር ሆኖ ቆሟል።

በየጊዜው አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት በብዙ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ተዓማኒነትን ያተረፈው ቡና ባንክ አ.ማ ከ12 ዓመታት በፊት ከ13 ሺ በላይ በሆኑ ባለአክሲዮኖች የተቋቋመ ና ከ300 በላይ በደረሱ ቅርንጫፎቹ በኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

በሃገሪቱ ከሚገኙ ባንኮች ውስጥ የብዙሃን ባንክ ተብሎ በመጠራት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ቡና ባንክ ከሚለይባቸው የባንክ አገልግሎቶች ዋናው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያማከለ፣ ፍላጎትና አቅማቸውን ያገናዘበ የልዩ ቁጠባና ብድር አገልግሎቶችን ማመቻቸት ነው።

Tags:

         ቡና ባንክ .

        BUNNA BANK S.C

  ለቡና ባንክ አ.ማ ባለአክስዮኖች በሙሉ

  ዕጩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትን ጥቆማ ለመቀበል ተሻሽሎ የወጣ ማስታወቂያ

  የቡና ባንክ አ.ማ የባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ታህሳስ 11 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው 11ኛ መደበኛ ስብሰባው ያቋቋመው “የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጥቆማና አስመራጭ ኮሚቴ” ከሐምሌ 01 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የዕጩ ጥቆማዎችን በመቀበል ላይ የሚገኝ ሲሆን የቦርድ አባላትን ለመጠቆም የሚያስችለውን የጥቆማ መሙያ ቅጽ ከቡና ባንክ አ.ማ ድረ-ገጽ https://www.bunnabanksc.com ወይም አዲስ አበባ ቦሌ መንገድ ሩዋንዳ መታጠፊያ የባንኩ ዋና መስሪያ ቤት 8ኛ ፎቅ ከሚገኘው የኮሚቴው ጽ/ቤት ወይም ከባንኩ ቅርንጫፎች ማግኘት ይቻላል፡፡

  ስለሆነም ባለአክስዮኖች ለዳይሬክተሮች የቦርድ አባልነት ብቁ የሆኑትን ፤ ለባንኩ ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችሉትን እና ከታች የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የሚያሟሉትን ዕጩዎች በቅፁ ላይ በጥንቃቄ በመሙላት እስከ ጥቅምት 01 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ብቻ ከላይ በተገለፀው የኮሚቴው ጽ/ቤት በአካል በማቅረብ ወይም አድራሻውን ለቡና ባንክ አ.ማ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጥቆማና አስመራጭ ኮሚቴ በማለት በባንኩ የፓ.ሣ.ቁጥር 1743 ኮድ 1110 በአደራ ደብዳቤ በመላክ ወይም የተሞላውን ቅጽ ስካን በማድረግ ለዚሁ ዓላማ በተዘጋጀው በባንኩ ኢሜይል bibnomination@bunnabanksc.com አያይዛችሁ በመላክ ለባንኩ ዕድገት የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

  ተጠቋሚ ዕጩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡-

  1. በዜግነት ኢትዮጵያዊ/ት ወይም የውጭ ሀገር ዜግነት ካለው/ላት በትውልድ ኢትዮጵያዊ/ት የሆነ/ች፤
  2. ዕድሜው/ዋ 30 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆነ/ች፤
  3. የዳይሬክተሮች የቦርድ አባል ሆኖ ቢመረጥ /ሆና ብትመረጥ ለመስራት ፈቃደኛ የሆነ/ች፤
  4. ከታወቀ የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ቢያንስ በመጀመሪያ ዲግሪ ወይም በአቻ የትምህርት ደረጃ የተመረቀ/ች፤
  5. የዳይሬክተሮች የቦርድ አባላት ስብስብ በባንክ ስራ፣ በፋይናንስ፣ በአካውንቲንግ፣ በማኔጅመንት፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሕግ፣ በቢዝነስ አስተዳደር ፣ በኦዲቲንግ ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ወይም በኢንቨስትመንት ማኔጅመንት መሠረታዊ ክህሎትን /ችሎታን ያካተተ እና የፆታ ስብጥርን ያገናዘበ ቢሆን ይመረጣል፤
  6. የፋይናንስ ድርጅት የቦርድ ዳይሬክተር ያልሆነ/ች ወይም ዳይሬክተሩ/ሯ 10% ወይም ከዚያ በላይ የባለቤትነት ድርሻ ያልያዘበት/ችበት የንግድ ድርጅት፤
  7. የማንኛውም ባንክ ተቀጣሪ ሠራተኛ ያልሆነ/ች፤
  8. የቡና ባንክ አ.ማ የዳይሬክተሮች ቦርድ ጥቆማና አስመራጭ ኮሚቴ አባል ያልሆነ/ች፤
  9. በግሉ/ሏ ወይም ሌላ ባለአክስዮንን በመወከል በቡና ባንክ አ.ማ ውስጥ ለተከታታይ ስድስት ዓመታት በቦርድ አባልነት አገልግሎ/ላ ከሆነ/ች ከለቀቀበት/ችበት ጊዜ ጀምሮ ስድስት ዓመታት ያለፈው/ፋት፤
  10. በብሔራዊ ባንክ እምነት መሰረት ታማኝ ፣ ሐቀኛ፣ ጠንቃቃ እና መልካም ዝና ያለው/ላት፤
  11. መልካም የፋይናንስ ታሪክና አቋም ያለው/ያላት ፤ የንግድ ሥራን ከመተግበር ወይም ድርጅትን ከመምራት አኳያ በፍርድ ቤት የመክሰር ውሳኔ ያልተላለፈበት/ባት፣ ከታክስ እና ከባንክ ክፍያዎች ጋር በተያያዘ ግዴታዎቹን/ቿን በአግባቡ የተወጣ/ች፤
  12. መልካም ስነምግባር ያለው/ላት፣ከዚህ በፊት በንግድ ማህበር አደራጅነት፣ ዳይሬክተርነት፣ ስራ አስኪያጅነት፣ተቆጣጣሪነት፣ኦዲተርነት ወይም በሌሎች የአመራር ኃላፊነቶች ላይ ተመድቦ/ባ ሲሰራ/ስትሰራ ከኃላፊነቱ/ቷ ጋር በተያያዘ ወይም በማናቸውም ሌላ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ በእምነት ማጉደል፣ በስርቆት ፣ በማጭበርበር፣ በውንብድና ወይም በሌላ ለቦርድ አባልነት ብቁ በማያደርግ ተመሳሳይ ወንጀል በፍ/ቤት ተከሶ/ሳ የጥፋተኝነት ውሳኔ ያልተሰጠበት/ባት፤
  13. ከመንግስት ባለስልጣናት መረጃን በመደበቅ፣ የተሳሳቱ የሂሳብ ወይም ሌሎች ሰነዶችን በመስጠት፣ የተቆጣጣሪ አካላትን ማረጋገጫዎች ባለመቀበል፣ መስፈርቶችን ባለማሟላት ፣ የእርምት ወይም የማስተካከያ እርምጃዎችን ባለመውሰድ ሪከርድ የሌለበት/ባት፤
  14. በኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገር በሚገኝ በማናቸውም በፈረሰ ባንክ ውስጥ ዳይሬክተር የነበረ/ች ከሆነ በቅድሚያ ከብሔራዊ ባንክ የጽሁፍ ፈቃድ ማቅረብ የሚችል/ ምትችል፤
  15. ዕጩ ተጠቋሚው በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው ድርጅት ከሆነ፤ ድርጅቱን ወክሎ የሚያገለግል ቋሚ ተወካይ (የተፈጥሮ ሰው) መመደብ ያለበት ሲሆን ይህ ተወካይ ሁሉንም መስፈርቶች ማሟላት ይጠበቅበታል፤
  16. መስፈርቱን የሚያሟሉ ሴት ዕጩዎች ይበረታታሉ፤

   

  ለበለጠ መረጃ ባለአክስዮኖች በስልክ ቁጥር 011-8-722845/011-1-264357 ደውለው ማብራሪያ ማግኘት ይችላሉ፡፡

   

  ማሳሰቢያ፤

  ኮሚቴው ከጥቅምት 01 ቀን 2014 . በኋላ የሚቀርቡ ጥቆማዎችን የማይቀበል መሆኑን ከወዲሁ ያሳስባል!!!

  NameDownloads
  እጩ መጠቆሚያ ቅጽ

  የቡና ባንክ አ.ማ

  የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት አስመራጭ ኮሚቴ

  Bunna Bank