Bunna Bank

የቡና ባንክ ባለአክሲዮኖች 16ኛ መደበኛ እና 7ኛ አስቸኳይ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ

ቡና ባንክ ዓመታዊ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔውን አካሄደ

  • በታሪኩ ከፍተኛ የሆነውን ከ2.6 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አስመዝግቧል፤
  • የአንድ አክሲዮን ትርፍ 146.7 በመቶ አድጓል ።
  • 5 ቢሊዮን ብር ዝቅተኛ የተከፈለ ካፒታል መጠንንአንድ ዓመት ቀድሞ አሳክቷል፡፡

ቡና ባንክ አ.ማ ዓመታዊውን የባለአክሲዮኖች 16ኛ መደበኛ ጠቅላላና 7ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን ቅዳሜ ህዳር 13ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተር አካሂዷል።  በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለአክሲዮኖች በታደሙበት በዚሁ ጉባዔ ላይ የቡና ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አስማረ የባንኩን እኤአ የ2024/25 የሂሳብ ዓመት ሪፖርት ለባለአክሲዮኖች አቅርበዋል።

በሪፖርቱ እንደተገለጸው፣ እኤአ በ2024/25 የሥራ ዘመን ባንኩን ወደ አዲስ የላቀ የአፈጻጸም ምዕራፍ ያሸጋገረ የፋይናንስ ውጤት መመዝገቡ ይፋ ተደርጓል። በዚህም ባንኩ በሂሳብ ዓመቱ ያጋጠሙ የኢኮኖሚ ውጥረቶችንና ተግዳሮቶችን በብቃት ተቋቁሞ፣ ከታክስ በፊት 2.627 ቢሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል፤ ይህም ከባለፈው ዓመት 930 ሚሊዮን ብር የትርፍ አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር የ182.5 በመቶ ዕድገትን የሚያንጸባርቅ ታሪካዊ ስኬታማ ውጤት ነው ተብሏል። በተጨማሪም፣ ባንኩ በሂሳብ ዓመቱ በአንድ ሺህ ብር አክሲዮን ላይ ያስመዘገበውን ትርፍ (Earnings Per Share) ባለፈው ዓመት ከነበረው 161.57 ብር የ146.7 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ወደ 398.65 ብር ከፍ ማድረግ ችሏል።

ከዚህ ታሪካዊ የትርፍ ብልጫ ባሻገር፣ ባንኩ የረጅም ጊዜ የፋይናንስ መዋቅራዊ ጥንካሬውን የበለጠ በማጎልበት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን የ5 ቢሊዮን ብር ዝቅተኛ የተከፈለ ካፒታል መጠን አንድ ዓመት ቀድሞ በማሳካት፣ የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 5.054 ቢሊዮን ብር በማድረስ የባንኩን የዕድገት መሠረት አጠናክሯል።

ይህንን የላቀ ውጤት ለባለአክሲዮኖች ይፋ ያደረጉት የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አስማረ፣ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት፣ “ይህ ስኬት የቡና ባንክ ጠንካራ የሥራ ባህልና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ ራዕይ ፍሬ ነው። የትርፍ መጠኑን ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ከማድረግ በተጨማሪ፣ ካፒታላችንን በማጎልበት ለባንካችን ቀጣይ አዳዲስ ፈጠራና መስፋፋት የሚሆን የማይናወጥ መሠረት መጣል ተችሏል” በማለት የሂሳብ ዓመቱን ስኬት ገልጸዋል።

በሪፖርቱ እንደተመለከተው፣ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ይህንኑ ጥንካሬ በሚያንጸባርቅ መልኩ በ20.3 በመቶ አድጎ 65.58 ቢሊዮን ብር ላይ ደርሷል። ከዚህ በተጓዳኝ ባንኩ ጠንካራ የሀብት ማሰባሰብ ሥራ በመሥራት ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘቡን በ16.7 በመቶ በማሳደግ 51.2 ቢሊዮን ብር ላይ አድርሷል። በተለይም 65.0 በመቶ የሚሆነው የተቀማጭ ገንዘብ የቁጠባ ሂሳብ መሆኑ፣ የባንኩን የገንዘብ ምንጭ መረጋጋትና ዘላቂነት በግልጽ ያሳያል ሲል ባንኩ አስታውቋል።

ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ባንኩ የገቢ ምንጮቹን በብቃት በማቀናጀት የባንኩ ጠቅላላ ገቢ በ46.2 በመቶ አሳድጎ 11.739 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎን የውጭ ምንዛሪ ግኝትንም በ16.5 በመቶ በመጨመር 195.2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መሰብሰብ መቻሉም በዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት ተጠቅሷል።

በተጨማሪም ባንኩ የብድር አቅርቦቱን በ9.8 በመቶ አሳድጎ 42.69 ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመክፈያ ጊዜ ያለፈባቸው ብድሮች ምጣኔ (NPL) ከብሔራዊ ባንክ የ5 በመቶ ገደብ በታች 4.09 በመቶ ሆኖ እንዲመዘገብ በማድረግ፣ የብድር አስተዳደር ጥራቱን አረጋግጧል ብለዋል የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ አስማረ በንግግራቸው ።

ሰብሳቢው አክለው እንደተናገሩት በዘመናዊ የባንክ አገልግሎት መስክ ቡና ባንክ የዲጂታል ሽግግሩን በማጠናከር፣ የሞባይል ባንኪንግ ግብይት መጠኑን ወደ 40.4 ቢሊዮን ብር ከፍ ያደረገ ሲሆን በተለይም በቅርቡ በጀመረው የዲጂታል ብድር አገልግሎት እስከ ጁን 30 ድረስ ብቻ 2.64 ቢሊዮን ብር ብድር በማቅረብ በገበያ ትስስሩ ያለውን የጎለበተ አቅም በተግባር አሳይቷል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር ቡና ባንክ ማህበራዊ ኃላፊነትን እንደ ወሳኝ ጉዳይ በመያዝ ለተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች በድምሩ 20.3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማበርከቱ ተጠቅሷል።

ቡና ባንክ በ2030 ከሃገሪቱ ግንባር ቀደም ሦስት የፋይናንስ ተቋማት አንዱ የመሆን ራዕዩን ለማሳካት ስትራቴጂያዊ እቅዱን በቁርጠኝነት መፈጸም መቀጠሉን አስታውቋል። በቀጣይ ዓመት የአደረጃጀት መዋቅር ለውጥን ማጠናቀቅ፣ የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶችን እና የብድር ተደራሽነትን ማስፋፋት፣ እንዲሁም የዋና መ/ቤት ሕንፃ ግንባታን በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ ማጠናቀቅ ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚሆኑ ሪፖርቱ ያሳያል።

አቶ ሙሉጌታ አስማረ የባንኩን ዓመታዊ አፈጻጸም አስመልክቶ በንግግራቸው እንደጠቀሱት፣ “በሂሳብ ዓመቱ የተመዘገበው ድል በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል ያለውን ጠንካራ ትብብር ማሳያ ነው ያሉ ሲሆን አክለውም ለጋራ ዕድገትና ብልጽግና በትጋት መስራታችንን ከምንጊዜውም በላይ አጠናክረን እንቀጥላለን” በማለት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በመጨረሻም የቦርድ ሊቀመንበሩ ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም የቡና ማህበረሰብ አባላት እጅ ለእጅ ተያይዘው ባንኩን ወደተሻለ ደረጃ ለማሻገር እንዲሰሩ የጠየቁ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደሁልጊዜው ሁሉ ለባንኩ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት በዘርፉ ጤናማ ውድድር እንዲኖር ስላደረገው ከፍተኛ አስተዋፅኦም አመስግነዋል፡፡

የባለራዕዮች ባንክ የሆነው እና ከተመሰረተ 16 ዓመታትን ያስቆጠረው ቡና ባንክ ከ14 ሺህ በላይ ባለአክሲዮኖችና ቁጥራቸው ወደ 4000 የሚጠጋ ቋሚ ሰራተኞች ያሉት በመላው የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ 454 ቅርንጫፎቹ የባንክ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ የሚገኝ ባንክ ነው።

 

                                                                      ሕዳር 13፣ 2018 ዓ.ም.

                                                                      ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽንስ ዳይሬክቶሬት

                                                                                          ቡና ባንክ

ለበጠ መረጃ

ኢሜይል: communications@bunnabanksc.com

ድረ-ገጽ: https://www.bunnabanksc.com

ስልክ፡ +251911403884፣ +251945598585

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This will close in 0 seconds

You cannot copy content of this page