New to site?


Login

Lost password? (X)

Already have an account?


Signup

(X)
Farooq

የቡና ባንክ ቺፍ ስትራተጂ ኦፊሰር አቶ መንክር ሃይሉ በመጀመሪያው ዙር የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች ይቆጥቡ ይሸለሙ የሽልማት ስነስርዓት ላይ ያደረጉት ንግግር

HomeNewsየቡና ባንክ ቺፍ ስትራተጂ ኦፊሰር አቶ መንክር ሃይሉ በመጀመሪያው ዙር የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች ይቆጥቡ ይሸለሙ የሽልማት ስነስርዓት ላይ ያደረጉት ንግግር
11
Oct
የቡና ባንክ ቺፍ ስትራተጂ ኦፊሰር አቶ መንክር ሃይሉ በመጀመሪያው ዙር የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች ይቆጥቡ ይሸለሙ የሽልማት ስነስርዓት ላይ ያደረጉት ንግግር
  • Author
    Genet Fekade
  • Comments
    0 Comments
  • Category

(ጥቅምት 01 ቀን 2014 ዓ.ም)

የተከበራችሁ በቡና ባንክ 1ኛ ዙር የመምህራን እና የጤና ባለሞያዎች ቁጠባና ሽልማት መርሃ ግብር  ተሳታፊ ደንበኞች ፣

የተከበራችሁ የቡና ባንክ የስራ አመራር አባላት፣ ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች

በቅድሚያ ባንካችን በሙያ ዘርፋችሁ ስም ባዘጋጀው የቁጠባ መርሃ ግብር ተሳትፋችሁ በመቆጠባችሁ ያዘጋጀነውን የማበረታቻ ሽልማት ያሸነፋችሁ ዕድለኛ ደንበኞቻችን እንኳን ደስ አላችሁ እያልኩ ሁላችሁም ጥሪያችንን አክብራችሁ በዚህ ፕሮግራም ላይ በመገኘታችሁ ምስጋናዬን ማቅረብ እወዳለሁ።

አንድ ሃገር ዕድገቷ ቀጣይ እንዲሆን ትምህርትና ጤና ዋና መሰረቶች ናቸው። ሃገር ጤናው የተጠበቀና በእውቀት የታነጸ ዜጋ እንዲኖራት በማድረግ በኩል ቀዳሚውን ሚና የሚጫወቱት በትምህርት እና በጤና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ናቸው።

መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች በድህነት አቅሟ ያስተማረቻቸውን ሃገራቸውን ውለታ ለመመለስ ባልተመቻቸ የመሰረተ ልማትና የኢኮኖሚ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ከገጠር እስከከተማ ለሚያበረክቱት የጎላ ድርሻ ቡና ባንክ ከፍ ያለ እውቅና ይሰጣል።

መምህራንና የጤና ባለሙያዎች ትውልድን በእውቀት የማነጽ እና የህዝብን ጤና የመጠበቅን ያህል ወሳኝና ከባድ ሃላፊነቶች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚሸከሙ ምሰሶዎች መሆናቸውንም ባንካችን በጽኑ ያምናል።

እነዚህ ባለሙያዎች እጅግ አድካሚና  ከፍተኛ ቁርጠኝነትን በሚጠይቅ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ትውልድንና ሃገርን ለማስቀጠል የሚተጉ እንቁ ዜጋዎች ናቸው። ሃገራቸው ሙያቸው የሚጥልባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ከባድ ሃላፊነት ጥላባቸዋለች።

ይህንን ግዴታቸውን በመወጣት ለህዝብ ከሚያበረክቱት ድርሻ ባሻገር ግላዊ ህይወታቸውን ለማሻሻል በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ቡና ባንክ አጋዠ ሆኖ በመምጣት የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያዳብሩና የነገ ህይወታቸውን እንዲቀይሩ ሁኔታዎችን አመቻችቶላቸዋል።

በዚህም ከስድስት ወራት በፊት ባንካችን የሃገር ባለውለታ በሆኑት እነዚህ ሁለት የሙያ ዘርፎች ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎችን ሁሉ ታሳቢ የደረገ የቁጠባና ሽልማት መርሃ ግብር አዘጋጅቶ ወደስራ አስገብቷል። በዚህ የቡና ባንክ የመጀመሪያ ዙር የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች የቁጠባ እና ሽልማት መርሃ ግብር በስድስት ወር ውስጥ ብቻ ከ66 ሺ በላይ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ይህ ከፍተኛ ተሳትፎ የዘርፉ ተዋንያን ቁጠባን ባህል በማድረግ እቅድና ራዕያቸውን ለማሳካት የሚያደርጉትን ጥረት በተጨባጭ ያሳየ ሲሆን ለባለሙያዎቹ የቁጠባ ልምድ መዳበር ባንካችን ሁኔታዎችን ማመቻቸቱም ተገቢና ትክክለኛ ተግባር መሆኑን አረጋግጧል።

ቡና ባንክም ለእነዚህ የሃገር ባለውለታዎች ከማበረታቻ ሽልማት ጋር የቁጠባ ባህላቸውን እያሳደጉ የባንኩ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የጀመረውን ተግባር በማጠናከር እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑባቸውን የባንክ አገልግሎቶች ለማቅረብ  በመስራት ላይ ይገኛል።

በዚህ የመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብር ላይ በሁሉም ደረጃ ላይ የሚገኙ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች ተካፋይ ሆነውበታል።

ይህ የመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብር ሲጠናቀቅ በብሄራዊ ሎተሪ ኣዳራሽ ይፋዊ የእጣ ማውጣት ስነስርአት የተካሄደ ሲሆን በቁጠባ አገልግሎቱ ላይ ሲሳተፉ ከቆዩ መምህራን እና የጤና ባለሞያዎች መካከል 55 ደንበኞች የተዘጋጁት እጣዎች አሸናፊ ሆነዋል።

በዚህ መሰረት በዛሬው ዕለት አንድ ዘመናዊ የ2020 ሞዴል ሱዙኪ ዲዛየር አውቶሞቢል ፣ 12 ዘመናዊ ላፕቶፖች፣ 12 ታብሌቶች፣ 24 ስማርት የሞባይል ስልክ ቀፎዎች፣ እንዲሁም ሙሉ ወጪያቸው የተሸፈነላቸው ስድስት የታሪካዊ ቦታዎች ጉብኝት ፓኬጆች ለአሸናፊዎች ይበረከታሉ፡፡

ለዚህ እድል የበቃችሁ ውድ ደንበኞቻችንን በባንካችን ማኔጅመንት እና ሰራተኞች ስም በድጋሚ እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡

ክቡራትና ክቡራን !

በኢትዮጲያ ውስጥ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚው ህብረተሰብ ቁጥር ከአጠቃላዩ ህዝብ አንጻር ሲለካ ያለው ክፍተት ሰፊ በመሆኑ የህዝቡን የባንክ አጠቃቀም ባህል ማሳደግ የባንኮችን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም አካላት ርብርብ የሚጠይቅ ሃላፊነት ነው። በአንጻሩም  ባንኮች ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ለሁሉም ተደራሽ የሆነ አገልግሎት በመስጠት ብዙሃኑን በባንክ ስርዓት ውስጥ ለማስገባት የሚያደርጉትን ጥረትም አጠናክረው የመቀጠል ግዴታ አለባቸው።

ቡና ባንክም በጥናት የተደገፉ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ ብዙሃኑን የህብረተሰብ ክፍል ወደባንክ ስርዓት እንዲገባና የቁጠባ ባህሉን በማሳደግ ህይወቱን እንዲያሻሽል የድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል።

የተከበራችሁ ተሸላሚ ደንበኞችና እንግዶች

ከ12 ዓመታት በፊት የተቋቋመና በመላው ሃገሪቱ 315 ቅርንጫፎች ያሉት ቡና ባንክ በየጊዜው አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት የደንበኞቹን ቁጥር ከ 1.5 ሚሊዮን በላይ ማድረስ ችሏል። ባንካችን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያማከለ፣ ፍላጎትና አቅማቸውን ያገናዘበ የልዩ ቁጠባና ብድር አገልግሎቶችን ማመቻቸቱ በብዙ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ተዓማኒነትን ለማትረፉ ዋነኛ ምክንያት ነው።

በቅርቡ ወደ ህዝብ መጓጓዣና የጭነት ትራንስፖርት ዘርፍ አንቀሳቃሾች ቁጠባ መርሃ ግብር ያሳደገው የታክሲና ባጃጅ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶችና ቁጠባና ሽልማት መርሃ ግብር ከፍተኛ የደንበኞች ቁጥር ያስመዘገበበት ቀዳሚው መርሃ ግብር ነው።ይህ ፕሮግራምም በርካታ ደንበኞችን በማፍራት የብዙሃኑን ህይወት መለወጥ ያስቻለ መሆኑ በደንበኞቹ  ተመስክሮለታል።

በተመሳሳይም ይህ የመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብሩ የተጠናቀቀው የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች ቁጠባ እና ሽልማት ፕሮግራም በርካቶችን የተመሳሳይ እድል ተቋዳሽ ያደርጋቸዋል የሚል እምነት አለን።

ከዚህ ሽልማት በኋላ ባንካችን ቆጣቢ ደንበኞቻችንን የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርገውንና በርካታ ሽልማቶችን የሚያስገኘውን ሁለተኛውን ዙር የመምህራን እና የጤና ባለሙያዎች ቁጠባና ሽልማት መርሃ ግብር በቅርብ ቀን ውስጥ ይፋ ያደርጋል።

ባንካችን ዜጎች ቁጠባን ባህል እንዲያደርጉ ከመደገፍና ከማነሳሳት ባሻገር በኢኮኖሚው ንቁ ተሳታፊ የሚሆኑበትን አቅም ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማረጋገጥ እወዳለሁ።

በመረጨሻም ዜጎች ቁጠባ የግል ህይወትን በእቅድ ከመምራትና ነገን የተሻለ ከማድረግ ባሻገር የሃገርን ኢኮኖሚ ለመገንባት ምሰሶ መሆኑን ተገንዝበው ከተረፋቸው ሳይሆን ካላቸው በመቀነስ ቁጠባን ባህል እንዲያደርጉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቀርባለሁ።

በመጨረሻም በዚህ መርሃ ግብር ለተሳተፋችሁ ደንበኞቻችን እና መርሃ ግብሩ የተሳካ እንዲሆን የየድርሻችሁን ለተወጣችሁ የስራ ክፍሎች በሙሉ የባለራዕዮች ባንክ በሆነው ቡና ባንክ የስራ አመራር አባላት ስም የላቀ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

Tags:

    Bunna Bank