New to site?


Login

Lost password? (X)

Already have an account?


Signup

(X)
Farooq

የቡና ባንክ ቺፍ ስትራተጂ ኦፊሰር አቶ መንክር ሃይሉ በመጀመሪያው ዙር የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች ይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ ግብር የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓት ላይ ያደረጉት ንግግር

HomeNewsየቡና ባንክ ቺፍ ስትራተጂ ኦፊሰር አቶ መንክር ሃይሉ በመጀመሪያው ዙር የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች ይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ ግብር የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓት ላይ ያደረጉት ንግግር
23
Sep
የቡና ባንክ ቺፍ ስትራተጂ ኦፊሰር አቶ መንክር ሃይሉ በመጀመሪያው ዙር የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች ይቆጥቡ ይሸለሙ መርሃ ግብር የዕጣ አወጣጥ ስነስርዓት ላይ ያደረጉት ንግግር
  • Author
    Genet Fekade
  • Comments
    0 Comments
  • Category

============

(መስከረም 11 ቀን 2014 ዓ.ም )

የተከበራችሁ የቡና ባንክ የስራ አመራር አባላት

የተከበራችሁ የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር የስራ ሃላፊዎች

ክቡራን የትምህርት እና የጤና ዘርፍ ባለሙያዎች ተወካዮች

እንዲሁም ይህንን ኹነት ለመዘገብ እዚህ የተገኛችሁ የሚዲያ ባለሙያዎች

በቅድሚያ ሁላችሁም ጥሪያችንን አክብራችሁ በዚህ ፕሮግራም ላይ በመገኘታችሁ ምስጋናዬን ማቅረብ እወዳለሁ።

እንደሚታወቀው ትምህርትና ጤና የአንድ ሃገር የዕድገት ማስቀጠያ ምሰሶዎች ናቸው።ሃገር ጤናማ ስርዓት ገንብታ ወደዕድገት የምታመራው አንድም በዕውቀት የታነጸ ፣ በሌላ በኩልም ጤናው የተጠበቀ ዜጋ ሲኖራት ነው። መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች ትውልድን በእውቀት የማነጽ እና የህዝብን ጤና የመጠበቅን ከባድ ሃላፊነት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የሚሸከሙ ምሰሶዎች መሆናቸውን ቡና ባንክ በጽኑ ያምናል።

መምህራንና የጤና ባለሙያዎች በዚህች ሃገር ነባራዊ ሁኔታ ብዙ ነገር ባልተመቻቸበት ፣ አድካሚ በሆነ ነገር ግን ከፍተኛ ቁርጠኝነትን በሚጠይቅ ስፍራ ሁሉ ተገኝተው ትውልድንና ሃገርን ለማስቀጠል የሚተጉ የዚህች ሃገር እንቁ ዜጋዎች ናቸው። ርቀት፣ ዘርና ቀለም ሳይወስናቸው በሁሉም አካባቢዎች ተገኝተው የሙያ ግዴታቸውን እንዲወጡ ሃገር ዜጎችን በእውቀት የማነጽ እንዲሁም ከበሽታ የመከላከል ከባድ ሃላፊነት ጥላባቸዋለች።

ቡና ባንክ የሃገር ባለውለታዎች ናቸው ብሎ የሚያምንባቸውን በእነዚህ ሁለት የሙያ ዘርፍ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች ታሳቢ የደረገ የመጀመሪያውን ዙር “የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች የቁጠባ እና ሽልማት መርሃ ግብር” ቀርጾ ላለፉት ወራት ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል።

በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መምህራንና የጤና ባለሙያዎች በቁጠባ መርሃ ግብሩ ላይ በመሳተፍ ባንኩ በስማቸው ለቀረጸው ፕሮግራም ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል። ይህ መርሃ ግብር ሲጀመር በርካቶች በባንካችን ማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ቡና ባንክ ሙያውን አክብሮ እና ባለሙያዎቹም የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስቦ ከማበረታቻ ሽልማቶች ጋር የጀመረው የቁጠባና ሽልማት መርሃ ግብር እንዳስደሰታቸውና በስማቸው በተቀረጸው ፕሮግራም ተሳታፊ ለመሆን እንዳላቅማሙ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ቡና ባንክም እነዚህ የሃገር ባለውለታዎች አንድም የቁጠባ ባህላቸውን እያሳደጉ የባንኩ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፣ በሌላ በኩልም በመቆጠባቸው ብቻ ተሸላሚ መሆን የሚችሉበት መርሃ ግብር ከመዘርጋት በተጨማሪ በተጠቃሚዎቹ አስተያየት በመበረታታት ቀጣይ ለነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሆኑ ልዩ ልዩ የባንክ አገልግሎቶችን ቀርጾ ተግባራዊ ለማድረግ በመስራት ላይ ይገኛል።

መርሃ ግብሩ በሁሉም ደረጃ ላይ የሚገኙ መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች ተካፋይ በሚሆኑበት እንደመሆኑ በመምህርነት ሙያ ላይ የተሰማሩና ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድረስ የሚያገለግሉ መምህራን ፣ እንዲሁም በትምህርት አስተዳደርና ድጋፍ ስራዎች ላይ የሚገኙ ሁሉ ተሳታፊዎች ሆነውበታል። በተመሳሳይም በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ ነርሶች፣ የጤና መኮንኖችና ጤና ረዳቶች፣ የማህበረሰብ ጤና ባለሙያዎች፣ የህክምና ዶክተሮች፣ ራዲዮሎጂስቶች እንዲሁም ከህክምና ሙያ ጋር ተያያዠነት ያላቸው ስራዎችን የሚያከናውኑ እና በህክምና ተቋማት ውስጥ በድጋፍ ሰጪነት የሚያገለግሉ ባለሙያዎች ሁሉ በዚህ የቁጠባና ሽልማት መርሃ ግብር ተሳታፊ ሆነዋል።

በቁጠባ አገልግሎቱ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ቁጠባውን እንደጀመሩ ተሸላሚ የሚያደርጋቸውን የዕጣ ቁጥር የተቀበሉ ሲሆን ከ ብር 400 ጀምሮ ሲቆጥቡ በእያንዳንዱ አራት መቶ ብር አንድ የሽልማት እጣ እንዲያገኙ ተደርጓል። በዚህም በርካቶች በቆጠቡት በርካታ ገንዘብ የዕጣ አሸናፊነት ዕድላቸውን ከፍ አድርገዋል።

በዚህ መሰረት በዛሬው ዕለት እዚህ አዳራሽ ውስጥ በሚካሄደው ይፋዊ የዕጣ ማውጣት ስነስርዓት ለነዚሁ የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች በሽልማት መልክ የተዘጋጁት አንድ ዘመናዊ 2020 ሞዴል ሱዙኪ ዲዛየር መኪና ፣ 12 ዘመናዊ ላፕቶፖችና 12 ታብሌቶች እንዲሁም 24 ስማርት የሞባይል ስልክ ቀፎዎች፣ እንዲሁም ሙሉ ወጪያቸው የተሸፈነላቸው ስድስት የታሪካዊ ቦታዎች ጉብኝት ፓኬጅ አሸናፊ እጣ ቁጥሮች ይፋ ይሆናሉ።በዚህም በርካታ ደንበኞቻችን የቁጠባ ባህላቸውን ከፍ ከማድረጋቸውና ለራዕያቸውና ግቦቻቸው እውን መሆን መሰረት ከመጣላቸው ባሻገር የተዘጋጁት ሽልማቶች አሸናፊ በመሆን በባንኩ ደንበኝነታቸው እርካታን ደስታ ያገኛሉ የሚል እምነት አለኝ።

ክቡራትና ክቡራን !

በኢትዮጲያ ውስጥ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚው ህብረተሰብ ቁጥር ከአጠቃላዩ ህዝብ አንጻር ሲለካ ያለው ክፍተት ሰፊ በመሆኑ የህዝቡን የባንክ አጠቃቀም ባህል ማሳደግ ከፍ ያለ ስራ የሚጠይቅ ሃላፊነት ነው። በአንጻሩም ባንኮች የሚሰጡት አገልግሎት ይህንን ክፍተት ለማጥበብ ወሳኝ በመሆኑ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና ለሁሉም ተደራሽ የሆነ አገልግሎት አሰጣጥን ማጠናከርም ግድ ነው።

ቡና ባንክም በየጊዜው በሚያካሂደው ጥናት ብዙሃኑን የህብረተሰብ ክፍል ወደባንክ ስርዓት እንዲገባ፣ በዚህም የቁጠባ ባህሉን በማሳደግ ህይወቱን እንዲያሻሽል ለማስቻል የተለያዩ አገልግሎቶችን እየቀረጸ ለጥቅም ሲያውል ቆይቷል።

ቡና ባንክ አ.ማ ከ12 ዓመታት በፊት የተቋቋመና ከ309 በላይ በደረሱ ቅርንጫፎቹ በኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ የግል ባንክ ሲሆን ከ13ሺህ በላይ በሆኑ ባለአክሲዮኖች ባለቤትነት የሚተዳደርና በሃገሪቱ ከሚገኙ ባንኮች ውስጥ የብዙሃን ባንክ ተብሎ በመጠራት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ የግል ባንክ ነው።

ባንኩ ከ 1.1 ሚሊዮን በላይ ለደረሱ ደንበኞቹ ቀልጣፋ የባንክ አገልግሎት በመስጠትና በየጊዜው አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት በብዙ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ተዓማኒነትን ያተረፈ ባንክ ሲሆን ከሚለይባቸው ተግባራት አንዱና ዋናው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያማከለ፣ ፍላጎትና አቅማቸውን ያገናዘበ የልዩ ቁጠባና ብድር አገልግሎቶችን ማመቻቸቱ ነው።

ላለፉት ዓመታት ተግባራዊ ካደረጋቸው መርሃ ግብሮቹ መካከል ቀድሞ የታክሲና ባጃጅ አሽከርካሪዎችና ባለንብረቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራ የነበረውና አሁን ወደ የብስ ትራንስፖርት ዘርፍ ያደገው “የህዝብ መጓጓዣ እና የደረቅና ፈሳሽ ጭነቶች ትራንስፖርት ዘርፍ ባለቤቶችና ባለንብረቶች የቁጠባና ሽልማት መርሃ ግብር” ቀዳሚው ተጠቃሽ ነው።

ይህ ፕሮግራምም በርካታ ደንበኞችን በማፍራት የብዙሃኑን ህይወት መለወጥ ያስቻለ መሆኑ በደንበኞቹ ተመስክሮለታል።በተመሳሳይም ይህ በመጀመሪያ ዙር መርሃ ግብሩ ፍጻሜ ላይ የምንገኘው የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች ቁጠባ እና ሽልማት ፕሮግራም በርካቶችን የተመሳሳይ እድል ተቋዳሽ ያደርጋቸዋል የሚል እምነት አለን።

ከዚህ ዕጣ መውጣት በኋላ በቅርቡ ከአሁኑ የላቁ ሽልማቶችን የሚያስገኘውን ሁለተኛውን ዙር የመምህራንና የጤና ባለሙያዎች የቁጠባ እና ሽልማት መርሃ ግብር ይፋ እናደርጋለን።

በዚህ አጋጣሚ ባንካችን ዜጎች ቁጠባን ባህል እንዲያደርጉ ከመደገፍና ከማነሳሳት ባሻገር በኢኮኖሚው ንቁ ተሳታፊ የሚሆኑበትን አቅም ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማረጋገጥ እወዳለሁ።

በመረጨሻም የባንኩን የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ጨምሮ ለዚህ ስራ ከስኬት መድረስ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ላበረከቱት የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር የስራ ሃላፊዎች የባለራዕዮች ባንክ በሆነው ቡና ባንክ ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

አመሰግናለሁ

Tags:

    Bunna Bank