New to site?


Login

Lost password? (X)

Already have an account?


Signup

(X)
Farooq

የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ

HomeNewsየቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ
21
Dec
የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ
  • Author
    Genet Fekade
  • Comments
    0 Comments
  • Category

•ባንኩ በበጀት ዓመቱ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ አትርፏል

•የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 13.88 ቢሊዮን ብር ደርሷል

•በአንድ አመት ብቻ ከሩብ ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል

•ለልማትና በጎ አድራጎት የ19 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል

የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የባለአክሲዮኖች 11ኛ መደበኛ እና 4ኛ ጠቅላላ ጉባኤ እሁድ ታህሳስ 11 ቀን 2013 ዓ.ም በጎልፍ ክለብ ተካሂዷል።

በጉባኤው ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለአክሲዮኖች የተገኙ ሲሆን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ዶክተር ሰውአለ አባተ የበጀት አመቱን ሪፖርት ለባለአክሲዮኖች አቅርበዋል።

ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው ባንኩ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከግብር በፊት ብር 582.042 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል ። በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 13.88 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉንም አስታውቋል፡፡

በዓመቱ ውስጥ የደንበኞቹን ቁጥር በ49.5 በመቶ በመጨመር ወደ 809 ሺህ 493 ከፍ ማድረግ እንደቻለም ተነግሯል።ባንኩ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአገር አቀፍ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረውን መቀዛቀዝ ተቋቁሞ አትራፊነቱን አስቀጥሎ መጓዙ የሚያበረታታ ውጤት መሆኑም በሪፖርቱ ተገልጿል።

በቀረበው ሪፖርት ላይ ይፋ እንደተደረገው ባንኩ እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 2020 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ 3.29 ቢሊዮን ብር ማሳደግ የቻለ ሲሆን ይህም የባንኩን አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 13.88 ቢሊዮን አድርሶታል ።

በቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ዶክተር ሰውአለ አባተ ለባለአክሲዮኖች የቀረበው ይኸው የበጀት አመቱ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ውስጥ የቁጠባ ሂሳብ 76 በመቶ የሚሆነውን በመሸፈን ከፍተኛ ድርሻ ይዟል ።ከአጠቃላይ የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ የተንቀሳቃሽ ሂሳብ የ19 በመቶ ድርሻ ሲይዝ በአንጻሩ የጊዜ ገደብ ተቀማጭ ደግሞ የ5 በመቶ ድርሻ እንደነበረውም በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል። ይህም ባንኩ አብዛኛውን ተቀማጩን አስተማማኝ ከሆኑት እና ብዙ ወለድ ከማያስወጡት የቁጠባ እና የተንቀሳቃሽ ሂሳቦች ላይ ማሰባሰቡን ያመለክታል ነው የተባለው ፡፡

በቦርድ ሊቀመንበሩ የቀረበው ሪፖርት የባንኩን የብድር አፈጻጸምም አብራርቶታል። በዚህ መሰረት ባንኩ በዓመቱ ውስጥ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በአጠቃላይ 3.29 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱ ተገልጿል። ይህም በአጠቃላይ ባንኩ የሰጠውን ብድር በ40 ከመቶ አሳድጎታል ተብሏል። ባንኩ በአጠቃላይ የሰጠው ብድር 11.57 ቢሊዮን ብር መድረሱም በሪፖርቱ ተካትቷል። ከዚህ ውስጥ ለገቢ እና የወጪ ንግድ የተሰጠው ብድር የ45 በመቶ ድርሻ በመያዝ ከፍተኛው ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ለግንባታ እና ኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰጠው ብድር 21 በመቶ፣ ለሃገር ውስጥ ንግድና አገልግሎት ዘርፍ የተሰጠው ብርድ ደግሞ 19 በመቶውን ድርሻ በመያዝ እንደደረጃቸው ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነዋል።

በዓመቱ ከተገኘው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሬ ውስጥ የወጪ ንግድ 111 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማስገኘት ቀዳሚ ሲሆን፣ ከውጭ ሀገር በሀዋላ እና በስዊፍት የተላከ ደግሞ 28.4 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለምአቀፍና ሃገር አቀፍ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ባሳደረው ተጽእኖ ሳቢያ ከውጭ ሃገር የሚላክ ሀዋላ መቀነሱ እንዲሁም የኤክስፖርት ስራ መቀዛቀዙ በውጭ ምንዛሪ ግኝት በኩል የባንኩን አፈፃፀም በተጠበቀው መልኩ እንዳይከናወን አሉታዊ ጫና እንዳሳደረ በሪፖርቱ ተብራርቷል።ባንኩ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ቁጥራቸው አስር ከሆኑ የውጭ ሃገራት ባንኮች ጋር የቀጥታ ግንኙት መስርቶ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ የገለፀው ሪፖርቱ ከተጨማሪ የዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር አብሮ ለመሥራት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

የባንኩን ጠቅላላ ሃብት የተመለከተ መረጃም በቦርዱ ሊቀመንበር ዶክተር ሰውአለ አባተ ሪፖርት ውስጥ ተካትቷል። እንደሪፖርቱ የባንኩ ሃብት በበጀት ዓመቱ የ4.37 ቢሊዮን ብር ዕድገት ያሳየ ሲሆን ጠቅላላ ሃብቱም ወደ 18.87 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ከባንኩ ጠቅላላ ሃብት ውስጥ የተጣራ ብድር 60.85 በመቶውን በመሸፈን ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል ሲል ነው ሪፖርቱ የገለጸው፡፡

የባንኩን ካፒታል በተመለከተ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት እንዳብራራው በበጀት አመቱ የብር 503.80 ሚሊዮን ብር እድገት አሳይቷል። ይህም የባንኩን አጠቃላይ የካፒታል መጠን 3.07 ቢሊዮን ብር አድርሶታል፡፡

የቦርዱ ሊቀመንበር ዶክተር ሰውአለ በሪፖርታቸው ስለባንኩ የቅርንጫፍ ማስፋትና የአዳዲስ ደንበኞች ማፍራት እንቅስቃሴዎችም ተናግረዋል። እንደገለጻቸው ቡና ባንክ ለደንበኞቹ ያለውን ተደራሽነት ብሎም የተቀማጭ ማሰባሰቡን ሥራ ለማሳደግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል በበጀት ዓመቱ 37 ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ ይህም ባንኩ በአጠቃላይ እኤአ እስከ ሰኔ 30 2020 የበጀት አመቱ መጨረሻ ድረስ ያሉትን ቅርንጫፎች መጠን 242 አድርሶታል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ምቹ አገልግሎቶችን በማቅረብ ደንበኞችን በማፍራት ረገድ ባንኩ በበጀት ዓመቱ የተቀማጭ ሂሳብ ደንበኞቹን ቁጥር በ268 ሺህ 070 በመጨመር የ49.5 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል። ይህም አፈጻጸም የባንኩን አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር በዓመቱ መጨረሻ ወደ 809 ሺህ 493 ከፍ አድርጎታል።

ከዚህ በተጨማሪም በበጀት አመቱ ባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ላይ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀሱን ሪፖርቱ አመልክቶ ካሉት ቅርንጫፎች መካከል በ200 ያህሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ የሚሰጥባቸው መስኮቶችን ከመክፈቱ በተጨማሪ አንድ ከወለድ ነፃ አገልግሎት ብቻ የሚሰጥ ቅርንጫፍ ከፍቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ በዋዲያና ቀርድ ከወለድ ነጻ ሂሳቦች 14,233 ደንበኞችን በመመዝገብ በአጠቃላይ 223.9 ሚሊዮን ብር የተቀማጭ ሂሳብ ለመሰብሰብ ችሏል ተብሏል፡፡

ሪፖርቱ በመጨረሻ በዋናነት ካካተታቸው አብይ ጉዳዮች መካከል የባንኩን የማህበራዊ ሃላፊነት የተመለከተው ሪፖርት ይገኝበታል። ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በሃገር ግንባታ እና የህዝብን ህይወት ለመለወጥና ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በሚካሄዱ ጥረቶች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን በበጀት አመቱ በድምሩ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ተጠቁሟል። ይህ ድጋፍ ወደፊትም የባንኩ አቅም በፈቀደ መጠን ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የቦርዱ ሊቀመንበር አረጋግጠዋል።ቡና ኢንተርናሽናል ባንክየባለራዕዮች ባንክ

Tags:

    Bunna Bank