New to site?


Login

Lost password? (X)

Already have an account?


Signup

(X)
Farooq

ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ነባር ባንኮች ጠንካራና ተወዳዳሪ ለመሆን ወደሚያስችላቸው ምእራፍ መሸጋገር አለባቸው አሉ

HomeNewsጠቅላይ ሚኒሰትሩ ነባር ባንኮች ጠንካራና ተወዳዳሪ ለመሆን ወደሚያስችላቸው ምእራፍ መሸጋገር አለባቸው አሉ
19
Oct
ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ነባር ባንኮች ጠንካራና ተወዳዳሪ ለመሆን ወደሚያስችላቸው ምእራፍ መሸጋገር አለባቸው አሉ
 • Author
  Genet Fekade
 • Comments
  0 Comments
 • Category
 • “ሁሉም ባንኮች በዘንድሮ ዓመት ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉ እንሰራለን”  
 • “20 አዳዲስ ባንኮች ፍቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ ናቸው”

ለአመታት በኢንደስትሪው ውስጥ የቆዩ ነባር ባንኮች ጠንካራ፣ እውነተኛ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ወደሚያስችላቸው ምዕራፍ መሸጋገር አንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አሳሰቡ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በተካሄደው አምስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛ ዓመት የስራ ዘመን አንደኛ ልዩ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው ይህንን የተናገሩት።

እንደጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ በዘንድሮ ዓመት መንግስት የባንኮቹን ካፒታል ጥናት ላይ በተመሰረተ ሁኔታ በማሳደግ  አንድ ምእራፍ እንዲያድጉ ይሰራል  ፡፡

ባለፈው የበጀት ዓመት በባንኮች ከተሰበሰበው ከ1 ትሪሊዮን ብር በላይ ሀብት ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው በአዲስ አበባና አካባቢው ይገኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ይህ አሃዝ በክልሎች በርካታ የባንክ ቅርንጫፎች መከፈት እንዳለባቸው አመላካች መሆኑን ጠቅሰዋል።

“እዚህ [አዲስ አበባ]  የተከማቸውን የባንክ አቅም ወደ ሁሉም የአገሪቱ ጫፎች በመውሰድ ትንሽም ቢሆን  ወደባንክ የሚገባው ተቀማጭ የገንዘብ መጠን  እንዲያድግ እና ለኢንቨስትመንት እንዲውል ያስፈልጋል” ነው ያሉት በማብራሪያቸው።

 የባንክ ቅርንጫፎች እየበዙ እና የቁጠባ መጠን እየጨመረ ሲሄድ ኢንቨስትመንት እንደሚያድግ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ስራ አጥነትን ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያነቃቀቃውም እንዲህ ያለው ተግባር መሆኑን ነው ያሰመሩበት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የባንኮች ቁጥር ማደግ ብቻ ሳይሆን የአንድ ባንክ የካፒታል መጠን መጨመር እና የመስራት አቅም መዳበር ወሳኝ ነው። ይህንን ለማረጋገጥም በዚህ ዓመት ባንኮች ካፒታላቸው ከፍ እንዲል እና ትልልቅ የሆኑ ባንኮች እንዲፈጠሩ እንሰራለን ነው ያሉት።

አክለውም ባንኮች ካፒታላቸውን እያሳደጉና የቁጠባ መጠንን እየጨመሩ ካልሄዱ አጠቃላይ ኢኮኖሚው እያደገ በሄደ ቁጥር ተጎጂ ሊሆኑ እንደሚችሉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስት ከፍተኛ ድጋፍ እና የፖሊሲ ማሻሻያ አሁን ለተመዘገበው የባንኮች እድገት  ተጠቃሽ ምክንያት ነው ይላሉ።

ለዚህ ማረጋገጫም ብሄራዊ ባንክ የግል ባንኮች የገንዘብ እጥረት እንዳያጋጥማቸው የ 14 ቢሊየን ብር ብድር መስጠቱን ጠቅሰዋል።

ላለፉት ጥቂት አመታት ባንኮች ከሚሰበስቡት ሀብት 27 በመቶ ቦንድ እንዲገዙ ይገደዱ እንደነበር ጨምረው ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህ አሰራር የባንኮችን ትርፋማነትን ስለቀነሰው በዘንድሮ አመት 27 በመቶ የቦንድ ግዢው እንዲቋረጥ መወሰኑን አንስተዋል።

“በቦንድ ግዢው የተሰበሰበው 15 ቢሊየን ብር ለባንኮች  እንዲለቀቅላቸው መደረጉ ከሌሎች የፖሊሲ እርምጃዎች ጋር ተዳምሮ የባንኩ ዘርፍ እየተነቃቃ እንዲመጣ አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል” በማለት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስታቸው ድጋፍ በባንክ ዘርፉ ላይ ስላስገኘው ውጤት ባብራሩበት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያሰመሩበት።

እንደጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጻ በያዝነው አመት ለብሄራዊ ባንክ የቀረቡ ወደ 20 የሚጠጉ አዳዲስ የባንክ ፍቃድ ጥያቄዎች በሂደት ላይ ናቸው፡፡ ከነዚህ ባንኮች አብዛኛዎቹ ቅድመ ሁኔታውን አሟልተው ወደ ኢንደስትሪው ከተቀላቀሉ በኢኮኖሚው ረገድ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅም  ጠ/ሚኒስትሩ በማጠቃለያቸው ተናግረዋል።

(ጥንቅር ፣ ኮ/ኮ/ፕ/ዋና ክፍል)

Tags:

  Bunna Bank