New to site?


Login

Lost password? (X)

Already have an account?


Signup

(X)
Farooq

News

ቡና ባንክ ከኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ (ከኮቪድ-19 )ጋር በተያያዘ የአገልግሎት ማሻሻያዎችን አደረገ

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ለደንበኞቹ ኮሮና ቫይረስ(ኮቢድ19) ወረርሽኝ እያስከተላቸው የሚገኙ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም የሚያስችሉ የተለያዩ የአገልግሎት ማሻሻያዎችንና የጥንቃቄ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

ቡና ባንክ ከአስከፊ በሽታው መስፋፋት ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተፈጠረውን ቀውስ ግምት ውስጥ በማስገባት ባንኩ ማሻሻያ ካደረገባቸው የባንኩ አገልግሎቶች መካከል የባንኩ ተበዳሪዎች የብድር ማራዘሚያ ክፍያ ኮሚሽን ይገኝበታል፡፡

በዚሁ መሰረት የባንኩ ተበዳሪ የሆኑ ደንበኞች ከዚህ ቀደም ይጠየቁ የነበረውን የብድር ማራዘሚያ ክፍያ ኮሚሽን ( የአገልግሎት ክፍያ) ከማርች 31 ቀን 2020 ጀምሮ ለቀጣይ ሁለት ወራት ሙሉ በሙሉ በማንሳት ለደንበኞቹ አጋርነቱን ገልጾአል፡፡

ባንኩ ተበዳሪዎች በኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ሳቢያ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ብድር የመክፈል አቅም ውስንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአገልግሎት ክፍያ በማሰቀረቱ ወረርሽኝ ምክንያት የሚደርሰውን የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ለመቀነስ ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን ሚና መጫወቱን ያመለክታል፡፡

ቡና ባንክ የአገልግሎት ፈላጊዎች መተፋፋግ ለማስቀረትና አካላዊ ርቀትን ተጠብቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ከማድረጉ ባሻገር በሞባይል ባንክ ፤በኢንተርኔት እና በቡና ኤቴኤም አገልግሎት በአንድ ጊዜ ሲሰጥ የነበረውን የገንዘብ መጠን እስከ አስር ሺ ብር ድረስ በማሳደግ እንዲያስተላልፉና እንዲገበያዬ ምቹ በማድረግ ደንበኞቹ ወደ ቅርንጫፎች መምጣት ሳያስፈልጋቸው በሞባይል፤በኤቴኤምና በፖስ የመክፈያ ማሽን እንዲጠቀሙ ማመቻቸቱን አስታውቋል፡፡

ባንኩ በተጨማሪም ቫይረሱን ስርጭቱን ለመግታት የሚያስችሉ ከደንበኞች አገልግሎት ጋር የተያያዙ ሰራተኞች የአፍ መሸፈኛ(ማስክ)፤የእጅ ጓንት እና ሳኒታይዘሮችን በማሰራጨት ርቀታቸውን ጠብቀው በጥንቃቄ አገልግሎቱን እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን አስረድቷል፡፡

በሌላ በኩል ባንኩ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን፤ነፍሰ ጡሮችንና እድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆኑ እንዲሁም የታወቀ የጤና ችግር ያለባቸው ሰራተኞች ሆኖ ከአፕሪል 1 ጀምሮ ለ14 ቀናት በቤታቸው እንዲቆዩ ወስኗል፡፡

/ News

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ. ከታክስ በፊት 625 ሚሊዮን ብር አተረፈ

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በተጠናቀቀው የ2011 የበጀት ዓመት ከታክስ በፊት 625 ሚሊዮን ብር ማትረፉን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢና ዋና ስራ አስፈጻሚ አስታወቁ፡፡

የቦርድ ሰብሳቢው ዶ/ር ሰውአለ አባተ እና ዋና ስራአስፈጻሚው አቶ ሙሉጌታ ዓለማየሁ ህዳር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ለባለአክሲዮኖች አስረኛ ጠቅላላ ጉባኤ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳስታወቁት፤ባንኩ ያገኘው የትርፍ መጠን ከካቻምናው በ198 ሚሊዮን ብር ወይም በ46.4 በመቶ ጭማሬ አስመዝግቧል፡፡

የባንኩ ውጤታማነት የተመዘገበው ባንኩ ሊቀነሱ የሚችሉ ወጪዎችን በጥንቃቄ በማስተዳደርና ያለውን ውስን ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል በተደረገው ጥረት መሆኑን የባንኩ ከፍተኛ ሃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡

በዚሁ መሰረት ባንኩ በበርካታ መስፈርቶች ከፍተኛ እድገት እንዳስመዘገበ ገልጸው፤የባንኩን ቀጣይ እድገት የሚያስቀጥሉና ተደራሽነቱን የሚያሰፉ 34 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት እንዲሁም አዳዲስ አገልግሎቶችን የሞባይል፤የኢንተርኔት፤የወኪል እንዲሁም ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትን በማስፋፋትና በማጠናከር በኩል ሰፊ ስራዎችን እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ባንኩ ቋሚ ሃብትን ለማፍራት ባደረገው ጥረትም በአዲስ አበባ እና በባህርዳር ከተሞች የራሱን ህንጻ በግዥ ባለቤት መሆን እንደቻለ የገለጹት የባንኩ ከፍተኛ ሃላፊዎች፤ የባንኩን የተከፈለ ካፒታሉን ወደ ብር 1.8 ቢሊየን ብር፤አጠቃላይ ሃብቱንም ወደ 14 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡

ባንኩ በአስር ዓመት ውስጥ ካስመዘገበው ውጤት የላቀ ውጤት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለማስመዝገብ የሚያስችል የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መነደፉን የገለጹ ሲሆን፤በተያዘው የበጀት ዓመት ወደ ትግበራ በመገባቱ በቀጣይ ዓመታት ዘርፍ ብዙ እመርታዎች እንደሚጠበቁ ከባንኩ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ 

/ News

ብሔራዊ ባንክ የአዲሱን የቡና ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመት አፀደቀ

ብሔራዊ ባንክ የአዲሱን የቡና ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመት አፀደቀ
ባለፈው ሳምንት ዕውቅና የተሰጣቸው የቀድሞ የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጭንቅል

ብሔራዊ ባንክ የአዲሱን የቡና ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመት አፀደቀ

ብሔራዊ ባንክ የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ ዓለማየሁ የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲያገለግሉ ከቦርዱ የቀረበለትን ጥያቄ በማየት ሹመታቸውን ማፅደቁ ተገለጸ፡፡

ከቡና ኢንተርናሽናል ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው አቶ ሙሉጌታ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲያገለግሉ በቦርዱ ታጭተው የብሔራዊ ባንክን ውሳኔ ሲጠባበቁ ነበር፡፡

ብሔራዊ ባንክ የአቶ ሙሉጌታ ሹመት ከማፅደቁ በፊት ከመስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት መሰየማቸው አይዘነጋም፡፡

አቶ ሙሉጌታ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ታደሰ ጭንቅልን ተክተው ነው፡፡ የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ አቶ ሙሉጌታን ሲሾም፣ አቶ ታደሰ ደግሞ የባንኩ አማካሪ እንዲሆኑ ሰይሟቸዋል፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው አቶ ታደሰ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ዕውቅና ከተሰጣቸው ሦስት የባንክ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ አዲሱ የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ19 ዓመታት ያገለገሉ ናቸው፡፡ እንደ ባንኩ መረጃ አቶ ሙሉጌታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሠርተዋል፡፡ በተለይ ወደ ቡና ባንክ ከመምጣታቸው በፊት በቺፍ ቢዝነስ ኦፊሰርነትአጠቃላይ የባንኩን እንቅስቃሴ በመምራት ስትራቴጂውን በመቅረጽ፣ ዘመናዊ የሥራ ሒደቶችን  በመንደፍ፣ ፖሊሲና መመርያዎችን በማዘጋጀት የባንኩን ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ ስኬታማ እንዲሆን አድርገዋል፡፡

ቀደም ሲልም በምክትል ፕሬዚዳንትነት የደንበኞች አካውንትና ትራንዛክሽን አገልግሎት ላይ የሠሩ ሲሆን፣ በምክትል ፕሬዚዳንት የፋይናንስ ዘርፉንም እንደመሩ የሥራ ልምዳቸው ያሳያል፡፡

አቶ ሙሉጌታ የባንኩ ቺፍ ሪስክና ኮምፖሊያንስ ኦፊሰር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአካውንት አናሊሲሲ በሥራ አስኪያጅነት፣ በብድር ኦዲት ቡድን መሪነት፣ በብድር ሞኒተሪንግ ኦፊሰርነት የሥራ ልምድ እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በቦርድ አመራርነትም በርካታ ድርጅቶችን እንደመሩ የሚያመለክተው የአቶ ሙሉጌታን የሥራ ልምድ የሚያሳየው መረጃ፣ የኮሜርሽያል ኖሚኒስ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ማገልገላቸው በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ የሲዳ ቴክስታይል ቦርድ ሰብሳቢ፣ የኢትዮጵያ ህዳሴ፣ የኢትዮጵያ ኮሞዲቲ ኤክስቼንጅና ሌሎችንም ድርጅቶች በቦርድ አመራርነት ማገልገላቸው የሥራ ልምዳቸው ያስረዳል፡፡

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በኢንዱስትሪው ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ የግል ባንኮች አንዱ ነው፡፡ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀለ ዘጠኝ ዓመታት የቆየ ሲሆን፣ከባንኩ ምሥረታ ማግሥት የመጀመርያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ሲመሩ የቆዩት አቶ ነገደ አበበ ናቸው፡፡ ከዚያም በመቀጠል አቶ እሸቱ ፋንታዬና ሦስተኛው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጭንቅል ሲሆኑ፣  አቶ ሙሉጌታ አራተኛው ዋና ሥራ አስፈጻሚ  ናቸው፡፡

ቡና ባንክ ከ175 በላይ ቅርንጫፎችን በመላ አገሪቱ የከፈተ ሲሆን፣ የባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ13 ሺሕ በላይና የካፒታል መጠኑም ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይመድረሱን ከባንኩ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽንና ፕሮሞሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

/ News

አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ የመልካም ምኞት መግለጫ ሰጡ

ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ሲገለገሉ ለቆዩ ደንበኞችና ለባንኩ ሰራተኞች አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ የመልካም ምኞት መግለጫቸውን አቶ ሙሉጌታ ዓለማየሁ ሰጡ፡፡

አቶ ሙሉጌታ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫቸው ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በአስቀማጭነት፤በተበዳሪነት፤በዓለም አቀፍ ንግድ በአስመጪነትና ላኪነት እንዲሁም በሃዋላና በመሳሰሉት የባንኩ አገልግሎቶች እየተጠቀሙ ላሉ ደንበኞች መጪው አዲስ ዓመት የሰላም ፤የብልጽግናና ከመቼውም ጊዜ በላይ ከባንካችን ጋር ስኬታማ ጉዞን የምትቀጥሉበት እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በአዲሱ ዓመት ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ተደራሽነቱን እያሳደገ፤ዘመናዊ አሰራርን እየተከተለ ቀልጣፋ አገልግሎቱን በተሻለ ብቃት እና ዘመናዊነትን በተላበሰ መልኩ በመስጠት  የስራችሁ  አጋርነቱ አጠናክሮ የሚቀጥልበት፤ለራዕያችሁ ስኬት በቅርበት የሚያገለግልበት  ዓመት ይሆናል ብለዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ ለባንኩ ሰራተኞች ባስተላለፉት መልዕክትም መጪው አዲስ ዓመት የባንካችንን አገልግሎት በአዳዲስ ቴክኖሎጂ የምናዘምንበት ፤የደንበኞቻችንን ጥያቄ በፈጣን አገልግሎት የምናረካበት ፤በኢንዱስትሪው ጠንካራ ተወዳዳሪ በመሆን ስኬትን የምንጨብጥበት እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

ስለሆነም የባንኩ ሰራተኞች በታታሪነትና በትጋት ደንበኞቻችንን በማገልገል ያቀድናቸውን እቅዶች ዳር ለማድረስ እንዲሁም በኢንዱስትሪው ውስጥ የበለጠ ተፎካካሪ እና ተመራጭ ባንክ የማድረግ ራዕያችንን እናሳካ  ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

/ News

ቡና ባንክ አቶ ሙሉጌታ አለማየሁን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሾመ

ቡና ባንክ አቶ ሙሉጌታ አለማየሁን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሾመ

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ሙሉጌታ ዓለማየሁ፣ የቡና ኢንተርናሽናል ባንክን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ የቡና ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሾመ ፡፡

የዳይሬክተሮች ቦርድ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የቆዩትን አቶ ታደሰ ጭንቅልን በአማካሪነት እንዲሰሩ እና አቶ ሙሉጌታ ዓለማየሁን ከመስከረም 1 ቀን 2018 ጀምሮ ባንኩን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ እንዲያደርጉት ሾሟቸዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ የቡና ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲያገለግሉ ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን ፤በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባገለገሉባቸው 19 ዓመታት የመጨረሻው የስራ ሃላፊነታቸው በቺፍ ቢዝነስ ኦፊሰርነት አጠቃላይ የባንኩን እንቅስቃሴ  በመምራት ስትራቴጂውን በመቅረጽ፤ዘመናዊ የሥራ ሂደቶችን በመንደፍ ፤ፖሊሰና መመሪያዎችን በማዘጋጀት የባንኩን እድገት በከፍተኛ ደረጃ ስኬታማ እንዲሆን አድርገዋል፡፡

ቀደም ሲልም በምክትል ፕሬዚዳንትነት የደንበኞች አካውንትና ትራንዛክሽን አገልግሎት ላይ የሰሩ ሲሆን፤በምክትል ፕሬዚዳንት የፋይናንስ ዘርፉንም እንደመሩ የስራ ልምዳቸው ይገልጻል፡፡

አቶ ሙሉጌታ ከሰሩባቸው ሰፊ የስራ ዘርፎች መካከልም ቺፍ ሪስክ እና ኮምፖሊያንስ ኦፊሰር ሆነው ከኖቨምበር 18 ቀን 2018 እስከ ፌብሪዋሪ 13ቀን 2013 ባንኩን ያገለገሉ ሲሆን፤በአካውንት አናሊሲሲ በስራ አስኪያጅነት፤በብድር ኦዲት ቡድን መሪነት፤በብድር ሞኒተሪንግ ኦፊሰርነት የስራ ልምድ እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በቦርድ አመራርነትም በርካታ ድርጅቶችን የመሩት አቶ ሙሉጌታ፤የኮሜርሽያል ኖሚኒስ ቦርድ ሰብሳቢ፤የሲዳ ቴክስታይል ቦርድ ሰብሳቢ፤የኢትዮጵያ ህዳሴ፤የኢትዮጵያ ኮሞዲቲ ኤክስቸንጅና ሌሎችንም ድርጅቶች በቦርድ አመራርነት መምራታቸውን የስራ ልምዳቸው ያስረዳል፡፤

ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ በኢንዱስትሪው ውስጥ ዘጠኝ ዓመታት የቆየ ሲሆን፣ በባንኩ ምሥረታው ማግሥት የመጀመርያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ሲመሩ የቆዩት አቶ ነገደ አበበ ሲሆኑ፤በመቀጠል አቶ እሸቱ ፋንታዬ  እና ሶስተኛው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጭንቅል ሲሆኑ ፤  አቶ ሙሉጌታ አራተኛው ዋና ስራ አስፈጻሚ  ይሆናሉ፡፡

ቡና ባንክ ከ175 በላይ ቅርንጫፎችን በመላ አገሪቱ የከፈተ ሲሆን፤የባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ13 ሺ በላይ እና የካፒታል መጠኑም ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ መድረሱን ከባንኩ የኮርፖሬት ኮምኒኬሽንና ፕሮሞሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

/ News

Bunna Bank