
ቡና ባንክ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን (ECMA) የሰነደ ሙአለነዋይ ምዝገባውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቀቀ
June 24, 2026
(አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17 ቀን፣ 2018 ዓ.ም.) ቡና ባንክ አ.ማ. የሰነደ ሙአለነዋይ ምዝገባን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን (ECMA) ፈቃድ ማግኘቱን በደስታ ይገልጻል። ይፋዊ ምዝገባው ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ይህም ስኬታማ ምዝገባ በባንኩ የኮርፖሬት እድገት እና እየተስፋፋ ባለው የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ውስጥ ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
በዚህ ኦፊሴላዊ ምዝገባ መሰረት የቡና ባንክ አ.ማ. 61,895,598 ነባር መደበኛ አክሲዮኖች፣ እንዲሁም ለነባር ባለአክሲዮኖች የሚቀርቡ 2,587,002 አዳዲስ መደበኛ አክሲዮኖች በባለስልጣኑ ጸድቀዋል፡፡
ይህ ስኬት ቡና ባንክ በኢትዮጵያ የሰነደ ሙአለነዋይ ገበያ (ESX) ውስጥ በቀጣይ ለመሳተፍ ላስቀመጠው እቅድ ወሳኝ እርምጃ ነው። ባንኩ ለግልጽነት፣ ለጠንካራ የኮርፖሬት ገቨርናንስ እና ለባለአክሲዮኖቹ ዘላቂ እሴት ለመፍጠር ያለውን ጠንካራ ቁርጠኝነት ያጎላ ተግባር ነው።
የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሙሉጌታ ዓለማየሁ በሰጡት መግለጫ"የሰነደ ሙአለነዋያችንን በካፒታል ገበያ ባለስልጣን (ECMA) በተሳካ ሁኔታ ማስመዝገባችን ለቡና ባንክ የሚያኮራ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው። ይህ ስኬታማ ክንውን የባንካችንን የወደፊት ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ የሚያንጸባርቅ፣ የገቨርናንስ ደረጃችንን የሚያሳድግ እና የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እያደገ ሲመጣ ለባለአክሲዮኖቻችን አዳዲስ እድሎችን የሚከፍት ነው። በዚህ ረገድ ባለአክሲዮኖቻችን እና ባለድርሻ አካላት ላሳዩን ቀጣይነት ያለው እምነት እና ድጋፍ ጥልቅ ምስጋናችንን እናቀርባለን።"
ባንኩ እንዳስታወቀው ከዚህ የአክሲዮን ጉዳይ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ መረጃዎችና ማብራሪያዎች በሂደት በይፋ የሚገለጹ ይሆናል።
በዚህ አጋጣሚ ቡና ባንክ ለኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን፣ ለክቡራን ባለአክሲዮኖቹ፣ ለደንበኞቹ እና ለሁሉም አጋሮቹ ላደረጉት የማያቋርጥ ድጋፍ የከበረ ምስጋናውን ያቀርባል።
ይፋዊ የአክሲየን ማህበሩን መግለጫ ሰነድ (Prospectus) ከዚህ በታች የሚገኘው ማስፈንጠሪያ በመጫን አውርደው ማንበብ ይችላሉ፡፡
https://bunnabanksc.com/ir_prospectus/bunnabank_prospectus/
ለተጨማሪ መረጃ፣ እባክዎ ያነጋግሩን፦
ስልክ፦ 8501