ቡና ባንክ አክስዮን ማህበር የኢንፎርሜሽን ደህንነት አስተዳደር ሲስተምስ (አይኤስኤምኤስ) ስታንዳርድ የሆነውን የISO/IEC 27001፡2022 ስታንዳርድ በተሟላ ሁኔታ በማሳካት ሰርተፍኬት ማግኘቱን ይፋ አድርጓል።
ይህ በዓለም-አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያለው ሰርቲፊኬሽን ባንኩ ያሉትን መረጃዎች ለመጠበቅ እና የደንበኞቹን እና የባለድርሻ አካላትን የመረጃ ደህንነት ደረጃውን በጠበቀ አሰራር ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ ያለውን የማያወላውል ቁርጠኝነት ያሳያል ተብሏል።
የ ISO/IEC 27001፡2022 የምስክር ወረቀት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመረጃ ደህንነት አስተዳደር መለኪያ ሆኖ የሚያገለግል የተመሰከረለት ሰርቲፊኬት መሆኑ ይታወቃል። ቡና ባንክ አ.ማ ይህንን የደህንነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማሳካት በመቻሉ ከሳይበር አደጋዎች የሚከላከሉ ጠንካራ የደህንነት ቁጥጥሮችን ተግባራዊ ለማድረግ ያለውን አቅምና ፍላጎት ያሳየ መሆኑ ተገልጿል።
የቡና ባንክ አ.ማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ ሰርቲፊኬቱን ሲቀበሉ እንደተናገሩት “ይህን የምስክር ወረቀት በማግኘታችን በጣም ተደስተናል፤ ይህ ፕሮጀክት የባንክ መረጃዎቻችንን ደህንነት የማስጠበቅ እርምጃዎቻችንን በቀጣይነት በማጎልበት የደንበኞቻችንን እምነት አስጠብቆ ለመቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት ያንፀባርቃል፤ ይህም ስኬታማ አፈጻጸም የቡድናችንን ጥረት እና ትጋት የሚያሳይ ነው። የባንክ ቢዝነስ ስራ ውጤት እና የአይቲ ደህንነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች በመሆናቸው ይህንን ሰርተፊኬት ማግኘታችን ትልቅ ስኬት ነው ” ብለዋል፡፡
ሰርቲፊኬሽን የሰጠው ሰርቲ-ትረስት ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ማይክ ካማው በበኩላቸው በፕሮግራሙ ላይ እንደተናገሩት ቡና ባናክ የሚጠበቅበትን ሁሉንም የሴኪዩሪቲ መስፈርቶች መቶ በመቶ ያሟላ የመጀመሪያው ተቋም ነው ያሉ ሲሆን ይህም ባንኩ ለኢንፎርሜሽን ሴኩዩሪቲ ማኔጅመንት ሲስተም የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ አስደናቂ ስኬት ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ባንኩ የባለራዕዮች ባንክ እንደመሆኑ ራዕዩን በዕውን እየተገበረ መሆኑን በግልጽ መናገር ይቻላል ብለዋል፡፡
ይህ አድካሚ የሰርተፊኬሽን ሂደት በርካታ የባንኩን የደህንነት ቁጥጥር ዘዴዎች ማለትም ተቋማዊ፣ ቴክኒካል፣ የአይቲ መሰረተ-ልማትና አስተዳደራዊ ቁጥጥር እና አሠራሮችን አጠቃላይ ግምገማ ያካተተ ነበር። የኦዲት ስራው የተከናወነው ገለልተኛ በሆነ ሰርቲፊኬሽን ሰጪ ድርጅት ሲሆን በስራውም ገለልተኛና የላቀ ሙያዊ አቅሙን በመጠቀም የባንኩን አሰራር እንዲገመግም ተደርጓል፡፡ በተሳካ ሁኔታ የተከናወነው ሰርቲፊኬሽን የቡና ባንክ አክሲዮን ማህበር የመረጃ ደህንነትን በተመለከተ ያለውን ቀድሞ በማሰብ ተገቢውን የጥንቃቄ እርምጃ የመውሰድ አካሄድ እና ሊከሰቱ የሚችሉ ስጋቶችን አስቀድሞ ለማስወገድ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
ቡና ባንክ ከኢንፎርሜሽን ደህንነት አስተዳደር ሲስተምስ ጋር ተያይዞ በርካታ የተለያዩ የተሻሻሉ የደህንነት እርምጃዎችን ተግባራዊ አድርጓል። ISO/IEC 27001፡2022 ሰርቲፊኬሽኑን ተከትሎ ባንኩ ከደንበኞች፣ የቢዝነስ አጋሮች እና ከተቆጣጣሪ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል ተብሎ ይታሰባል። የእውቅና ማረጋገጫው ባንኩ ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለመጠበቅ እና ተያያዥ አደጋዎችን ለመቀነስ ሁሉንም አስፈላጊ የጥንቃቄ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው ተብሏል። ይህም በመሆኑ የባንኩ ደንበኞች መረጃቸው በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ደህንነት እንደተያዘ እምነት እንዲኖራቸው ያደርጋል።
ቡና ባንክ አክስዮን ማህበር ያስመዘገበው ይህ ስኬት በአገራችን የባንክ ዘርፍ የመረጃ ደህንነትን በማስፈን ደረጃውን ከፍ ያደረገ አሰራር ሲሆን ባንኩን በፋይናንሺያል ሴክተሩ የሳይበር ደህንነት ጥበቃ ረገድ ግንባር ቀደም አድርጎታል ማለት ይቻላል። ባንኩ በመረጃ ደኅንነት ግንባር ቀደም ሆኖ መቀጠሉን በማረጋገጥ በዘመናዊ የደህንነት ቴክኖሎጂዎች እና አሰራሮች ላይ ኢንቨስት ማድረጉን እንደሚቀጥል አሳውቋል።
