ከግብር በፊት ብር 930.1 ሚሊዮን ብር አትርፏል ።
የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ብር 54.53 ቢሊዮን ደርሷል፡፡
የተቀማጭ ደንበኞቹን ቁጥርም 4, 019, 072 ማድረስ ችሏል።

ቡና ባንክ አ.ማ ዓመታዊውን የባለአክሲዮኖች 15ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እሁድ ታህሳስ 6 ቀን 2017 ዓ.ም አካሂዷል።
በአዲስ ፓርክ ሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደውና በርካታ ቁጥር ያላቸው ባለአክሲዮኖች በታደሙበት በዚሁ ጉባዔ ላይ የቡና ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አምባሳደር ዓለማየሁ ሰዋገኝ የባንኩን የ2023/24 ዓመታዊ ሪፖርት ለባለአክሲዮኖች በንባብ አቅርበዋል።
ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው ባንኩ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከግብር በፊት 930.1 ቢሊየን ብር ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን በቀረበው ሪፖርት ላይ ይፋ እንደተደረገው ባንኩ እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 2024 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ካለፈው በጀት ዓመት 20 በመቶ ዕድገት በማሳየት 43.87 ቢሊዮን ብር ሊደርስ ችሏል። ከዚህም በበጀት ዓመቱ ከተሰበሰበው አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ውስጥ ከቁጠባ ሂሳብ 2.79 ቢሊዮን ብር ፣ ከተንቀሳቃሽ ሂሳብ 1.55 ቢሊዮን ብር ፣ ከጊዜ ገደብ ተቀማጭ 2.62 ቢሊዮን ብር ያገኘ ሲሆን ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትም 307.0 ሚሊዮን ብር ድርሻ እንዳለቸው ሪፖርቱ ያሳያል።
አምባሳደር ዓለማየሁ በንግግራቸው እንዳሰመሩበት ከሆነ ባለፈው የበጀት ዓመት እንደሃገር በተከሰተው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ተደራራቢ የሆኑ የተቆጣጣሪ አካላት መመሪያዎች መውጣትና ተግባራዊ መሆን፣ እንዲሁም በተለያዩ ክልሎች የተከሰቱ ግጭቶችና ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የፈጠረው የኑሮ ውድነት ሳቢያ የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ ተግዳሮት ተጋርጦበት ነበር ያሉ ሲሆን እነዚህ ችግሮች የባንኮችን የማበደር ብቻ ሳይሆን ተቀማጭ የማሰባሰብ እንቅስቃሴም በእጅጉ ፈትነውታል። ይህም በውጤቱ የባንኮችን የመክፈል እና የማበደር አቅም በእጅጉ ተፈታትኖታል።
አክለውም ይሁንና ባንካችን በኢንደስትሪው ላይ የተጋረጡትን ፈተናዎች ተቋቁሞ በዚህ ጠንካራ ውድድር ውስጥ መዝለቅ በመቻሉም አትራፊነቱን አስጠብቆ ቀጥሏል ብለዋል።
በቦርድ ሊቀመንበሩ የቀረበው ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው ባንኩ በዓመቱ ውስጥ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በአጠቃላይ 4.1 ቢሊዮን ብር አበድሯል። ይህም ቡና ባንክ በአጠቃላይ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ያበደረውን የገንዘብ መጠን በ11.8 በመቶ በማሳደግ 38.87 ቢሊዮን ብር አድርሶታል።
ከውጭ ሃገር የሚላክ ሀዋላ ከላይ በተገለጹት ዓለምአቀፋዊና ሃገራዊ ችግሮች ባስከተሉት ተጽእኖ ሳቢያ መቀነሱ እንዲሁም የኤክስፖርት ስራ ጉልህ በሆነ መልኩ መቀዛቀዙ በውጭ ምንዛሪ ግኝት በኩል የባንኩን አፈፃፀም በታቀደው መልኩ እንዳይከናወን አሉታዊ ጫና ያሳደረ ሲሆን የቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት በዓመቱ የባንኩ የውጭ ምንዛሬ ግኝት 167.6ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መሆኑንም ጠቁሟል።
ያለፈው ዓመት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ኢንደስትሪው ላይ የፈጠረው ጫና የባንኩን የውጭ ምዛሬ ግኝቱን ያሳነሰው ቢሆንም በቀጣይ የደንበኞቹን ፍላጎት በማርካት የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን በበለጠ ለማሳደግ ካለው ፍላጎት አንፃር ከታወቁ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች እና ባንኮች ጋር የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሪፖርቱ አመልክቷል።
በቦርዱ ሊቀመንበር አምባሳደር ዓለማየሁ ሰዋገኝ ሪፖርት ውስጥ ከተካተተው አንዱ የባንኩን ጠቅላላ ሃብት የተመለከተ መረጃ ሲሆን እንደሪፖርቱ የባንኩ ጠቅላላ ሃብት በበጀት ዓመቱ የ8.14 ቢሊዮን ብር ዕድገት አሳይቶ 54.53 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
ሊቀመንበሩ ባቀረቡት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት እንደተብራራው የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በበጀት ዓመቱ የብር 549.2 ሚሊየን ብር እድገት አሳይቷል። ይህም የባንኩን አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታል መጠን 4.83 ቢሊዮን ብር አድርሶታል፡፡
በቀረበው ሪፖርት ቡና ባንክ ለደንበኞቹ ያለውን ተደራሽነት ብሎም የተቀማጭ ማሰባሰቡን ሥራ ለማሳደግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል ምቹ የባንክ አገልግሎቶችን በማቅረብና አዳዲስ ደንበኞችን በማፍራት ረገድ በተደረገው እንቅስቃሴ ባንኩ በበጀት ዓመቱ የተቀማጭ ሂሳብ ደንበኞቹን ቁጥር በ 968,819 ከፍ በማድረግ የ31.8 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉም ተብራርቷል። ይህም አፈጻጸም የባንኩን አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ወደ 4,019,072 ከፍ አድርጎታል።
የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎትን በተመለከተ በ2023/24 በጀት ዓመት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የባንኩ ቅርንጫፎች፣ ሆቴሎች፣ እና የንግድ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ላይ የተተከሉ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች ቁጥር 200 ደርሷል። በተመሳሳይም ሪፖርቱ እንደጠቆመው የባንኩ አጠቃላይ የካርድ ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥር 413,892 የደረሰ ሲሆን በባንኩ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች በበጀት ዓመቱ 1.39 ቢሊየን ብር ማንቀሳቀስ መቻሉም ተጠቁሟል። በተያያዘ የሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥር ማደጉን ፣ በዚህም በድምሩ 21.1 ቢሊየን ብር በላይ የገንዘብ ልውውጥ መደረጉን ሪፖርቱ ገልጻል፡፡
ቡና ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የራሱ ልዩ መለያ እና የንግድ ስም እንዲኖረው በማስቻል “ኻዲም” (KHADIM)” የተሰኘ የአገልግሎት መለያ በመያዝ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ስራ መስራት መቻሉን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ ይህም በባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተገኘውን አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ብር 1.93ቢሊዮን አድርሶታል ብሏል ሪፖርቱ።
ሪፖርቱ በዋናነት ካካተታቸው አብይ ተግባራት መካከል ስጋት ተጋላጭነትን መቋቋም እና ኮምፕሊያንስን በሚመለከት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባቀመጠው መስፈርተ መሰረት ከኮርፖሬት ቢዝነስ ስትቴጂው ጋ የሚጣጣም ይስጋ አስተዳደር ፐሮግራም መተግበሩ የተገለጸ ሲሆን እ.ኤ.አ ከ2023-2007 የባንኩን የአምስት ዓመት ኮርፖሬት ስትራቴጂክ ዕቅድ፣ የሰው ሀብት ስትራቴጂ፣ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስትራቴጂዎችን ማጽደቁም ተገልጿል።
የቦርድ ሊቀመንበሩ እንደተናገሩት ባንኩ ቀጣይ የባንኩ ስትራቴጂያዊ የትኩረት አቅጣጫዎችነ የተቀሱ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የአምስት ዓመቱን ኮርፖሬት ስተራጂክ ዕቅድ ትግበራ መከታተል፣ የሀብት ማሰባበሰብ ስራን ማጠናከር የዲጂታል ባንክና የአይቲ ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን ማስፋፋትና ሌሎችም እንደሚገኙበት ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
በመጨረሻም የቦርድ ሊቀመንበሩ ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም የቡና ኮሚዩኒቲ አባላት እጅ ለእጅ ተያይዘው ባንኩን ወደተሻለ ደረጃ ለማሻገር እንዲሰሩ የጠየቁ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደሁልጊዜው ለባንኩ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት በዘርፉ ጤናማ ውድድር እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን በማመስገን ሁሉም የቡና ኮሚዩኒቲ ይህንኑ ስኬታማ ጉዞ ለማሳካት እንዲሰራ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የባለራዕዮች ባንክ የሆነው እና ከተመሰረተ 15 ዓመታትን ያስቆጠረው ቡና ባንክ ከ14 ሺህ በላይ ባለአክሲዮኖችና ከ4100 በላይ ቋሚ ሰራተኞች ያሉት በመላው የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ 474 ቅርንጫፎቹ የኮንቬንሽናል፣ ዲጂታል አንዲሁም ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ባንክ ነው።



















