
- ለሴት ተማሪዎችና ለትምህርት ቤቶች ድጋፍ ይደረጋል
- ሴት መሪዎችን ለማብቃት ስልጠና ተካሂዷል
ቡና ባንክ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን (ማርች 8) ምክንያት በማድረግ፣ የሴት ሰራተኞቹን ሙያዊ ብቃት ወደ ላቀ የአመራር እርከን የሚያሸጋግር ስልጠና ከማካሄዱም በላይ፣ ተቋማዊ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣትም በበርካታ ትምህርት ቤቶች በመገኘት ሴት ተማሪዎችን የመደገፍና የማበረታታት እንዲሁም ለትምህርት ቤቶች እገዛ የማድረግ መርሃ ግብርም ያካሂዳል፡፡
ከዚህ ባሻገርም የባንኩን እና አጋሮቹን ግንኙነት የሚያጎለብት የደንበኞች ጉብኝትና የአገልግሎት ማስፋት ዘመቻ በይፋ አስጀምሯል።
ባንኩ ከካፒታል የፋይናንሺያል የልህቀት ማዕከል (CFEC) ጋር በመተባበር ከየካቲት 25 እስከ 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት ያካሄደው “የሴቶች አመራርና የሙያ እድገት” ስልጠና፤ ከዋናው መስሪያ ቤት እስከ ቅርንጫፍ ያሉ ሴት አመራር ሰራተኞች በስትራቴጂካዊ ውሳኔ አሰጣጥ፣ በተፅዕኖ ፈጣሪ ተግባቦትና በራስ መተማመን ዙሪያ የላቀ ክህሎት እንዲጨብጡ አስችሏል። ይህ መርሃ ግብር ተሳታፊዎቹ ለቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚሆን ግልጽ የሙያ እድገት ራዕይ እንዲሰንቁ ከማድረጉም ባለፈ፣ ሴቶች ያላቸውን እምቅ አቅም ለተቋማዊ ስኬት እንዲያውሉ የሚያነቃቃ መድረክ ሆኖ ተጠናቋል።
ይህንኑ የውስጥ አቅም ግንባታ መነቃቃት ወደ ደንበኞች አገልግሎት በማሸጋገር፣ ባንኩ “የማርች 8 የደንበኞች ግንኙነት እና የሽያጭ ዘመቻ” በሚል ታላቅ እንቅስቃሴ መጀመሩን በይፋ አብስሯል። ይህ ዘመቻ ማርች 8ን አጋር ደንበኞችን በማመመስገንና ግንኙነቶቻችን ይበልጥ በማጠናከር ለማክበር የታለመ ሲሆን፤ በተለይም በችርቻሮ (Retail)፣ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች (SME) እንዲሁም በኮርፖሬት የደንበኞች ዘርፍ ላይ ልዩ ትኩረት ያደርጋል።
ዘመቻው የዲጂታል ባንክ አገልግሎት አጠቃቀምን ማሳደግ፣ አዳዲስ ደንበኞችን ማፍራት እና የባንኩን የማህበራዊ ሚዲያ ተደራሽነት ከማጠናከር ጎን ለጎን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በመገኘት የትምህርት አጋዠ ቁሳቁሶችን እገዛና ሴት ተማሪዎችን ለማበረታታትም ልዩ ልዩ ድጋፍ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡
በአጠቃላይ ቡና ባንክ የሴት ሰራተኞቹን የውሳኔ ሰጪነት ሚና ማጎልበትን ከቢዝነስ ስኬቱ ጋር በማስተሳሰር፣ ለሥርዓተ-ጾታ እኩልነትና ለተቋማዊ እድገት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት በተግባር እያሳየ ይገኛል።
ባንኩ የሰራተኞቹን ብቃት በማሳደግና የደንበኞቹን እምነት በማዳበር፣ ውጤታማ የሀብት ማሰባሰብ ስራንና ዘላቂ የንግድ እድገትን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ድጋፍና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡
