- ለደንበኞቹ የአለምአቀፍ ክፍያ ስርዓት አማራጮችን አስፍቷል

የዲጂታል መዳረሻዎቹን በየጊዜው በማስፋት የደንበኞቹን ፍላጎት በማሟላት ላይ የሚገኘው ቡና ባንክ የአለምአቀፍ ቪዛ ካርድ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ይፋ አድርጓል።
ዛሬ ታህሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ባንኩ ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደ ስነስርዓት ቡና ባንክ የቪዛ ኢንተርናሽናል አባል መሆኑንና የቪዛ ካርድ አገልግሎቶችን መስጠት በይፋ መጀመሩን አብስሯል።
ቡና ባንክ የአምስት አመት የዲጂታል ስትራተጂ ቀርጾ ወደስራ ከገባ አንድ አመት እንደሞላውና ይህ አዲስ አገልግሎትም የዚሁ ስትራቴጂ አካል መሆኑ በማስጀመሪያ ስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል።
ቡና ባንክ በቀረጸው የዲጂታል መሪ ዕቅድ የክፍያ መዳረሻዎችን በመጨመርና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓቶች ጋር በመተባበር ለደንበኞቹ አዳዲስ አማራጮችን በማቅረብ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡ በዚህ መሰረትም ቡና ባንክ ከነዚህ አለምአቀፍ የክፍያ ስርዓት አሳላጮች መካከል ቀዳሚ ከሆነውና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባለው ቪዛ ኢንተርናሽናል (Visa International) አባል በመሆን የቪዛ ካርድ አገልግሎት መስጠት መጀመሩም ተገልጿል።
የቡና ባንክ ቡና ባንክ ይህን መስተጋብር መጠቀሙ የክፍያ ካርድ ለደንበኞች ማቅረብ እንዲሁም አለምዓቀፍ የክፍየ ካርድ መቀበል አስችሎታል ፡፡
ቡና ባንክ ከሚሰጣቸው የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶች በተጨማሪ በነጋዴ መዳረሻዎች (Merchant ) የቪዛ ኢንተርናሽናል ካርዶችን መቀበል መቻሉ ለሀገር ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት የሚያስችለው መሆኑም ተጠቁሟል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የብሄራዊ ባንክ በቅርቡ ያወጣውን የውጭ ምንዛሬ አፈፃፀም መሰረት በማድረግ ለትምህርት፣ ለጉብኝት እንዲሁም ለህክምና ወደውጭ ሀገር ለሚጓዙ መንገደኞች የውጭ ምንዛሬ በክፍያ ካርድ መስጠት መጀመሩም ተገልጿል።
ይህ ሂደት ባንኩ ከዚህ ቀደም በእጅ ይሰጥ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ በካርድ በመስጠት ደንበኞቹን የተሻለ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ነው የተባለው፡፡ ይህም በክፍያ መቀበያ ማሽን፣ በኦንላይን(e-commerce) እንዲሁም በተለያዩ ከንክኪ ነፃ በሆኑ መዳረሻዎች በቀላሉ ክፍያዎችን መፈፀም ያስችለዋል ነው የተባለው።
ባንኩ አዲስ ያስተዋወቀው የክፍያ ካርድ የቪዛ እውቅና ያለው በመሆኑ በንክኪም ሆነ ከንክኪ ውጭ የሚሰራ እንደሆነም ተጠቁሟል። ቡና ባንክ ከዚህ በኋላ ለሀገር ውስጥ አገልግሎት የሚያቀርቧቸው የክፍያ ካርዶች የቪዛ መገለጫ ያላቸው በመሆኑ የክፍያ ካርድ ቁጥራቸውን በመጠቀም ከውጭ ሀገር ገንዘብ መቀበልና በቀላሉ ወደ ደንበኛው ሂሳብ ማስገባት ወይም መላክ የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ደንበኞች እነዚህን ካርዶች በመጠቀም የተመረጡ የኦንላይን ግብይቶችንም መፈፀም እንደሚያስችላቸው በስነስርዓቱ ላይ ተነግሯል።
ቡና ባንክ ከቪዛ ኢንተርናሽናል ጋር መስተጋብር በመፍጠሩ ለነጋዴዎች አማራጭ የክፍያ ስርዓት ከመዘርጋት በተጨማሪ በባንኩ ቅርንጫፎች ወይም በአቅራቢያ ባስቀመጣቸው የኤ.ቲ.ኤም ማሽኖች አለምአቀፍ የቪዛ ኢንተርናሽናል ካርዶችን መቀበል መቻሉም ተገልጿል ።

















