ቡና ባንክ በርካታ የባንክ አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ ለማከናወን የሚያስችለውን የዲጂታል ደንበኞች ምዝገባ ስርዓት (Digital Customer Onboarding System) ዛሬ በይፋ ወደ ስራ ማስገባቱን አስታውቋል።
ይህ በድረ-ገጽ (Web-based) ላይ የተመሰረተ የአሰራር ስርዓት ደንበኞች በአካል ወደ ቅርንጫፍ መሄድ ሳያስፈልጋቸው ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ቆጥበው ባሉበት ሆነው የባንክ ሂሳብ እንዲከፍቱ እና የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።
ይህ ዘመናዊ ትግበራ የባንኩ የ “Vision 2030” ስትራቴጂክ እቅድ አካል ሲሆን፣ ባንኩን በቅርንጫፍ ላይ ከተመሰረተ አሰራር ወደ ተማከለ እና ዲጂታል-መር የፕላትፎርም (Platform) ስርዓት ለማሸጋገር የሚረዳ ጭምር ነው።
ዋና ዋና ቴክኒካዊ ፋይዳዎች፡
-
- የርቀት ምዝገባ (Remote Onboarding) ፡ ደንበኞች ደህንነቱ በተጠበቀ የድረ-ገጽ መተግበሪያ (https://onboardingportal.bunnabanksc.com/ ) አማካኝነት ሙሉ የባንክ ሂሳብ የመክፈት ሂደትን ከጅምሩ እስከመጨረሻው (End to End) ማከናወን ይችላሉ።
-
- የአገልግሎት አውቶሜሽን (Service Automation) ፡ ከሂሳብ መክፈት ባሻገር የዚህ አገልግሎት ትልቁ ፋይዳ ተጠቃሚዎች የኤቲኤም ካርድ ለማዘዝ፣ የሞባይል ባንኪንግ ለማስጀመር እና ከባንኩ ባለሙያዎች ጋር ቀጠሮ ለመያዝ በዲጂታል መንገድ ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ።
-
- አቅጣጫ ጠቋሚ (Geolocation Tools) ፡ ቅርንጫፎችን፣ ኤቲኤምና (ATM) አይቲኤሞችን (ITM)እንዲሁም የባንኩ የክፍያ አማራጭ ያለባቸውን የንግድ ቦታዎች ለማግኘት የሚያስችል የካርታ (Map) ትስስርን ያካተተ ነው።
-
- የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ትስስር (Fayda ID Integration) ፡ ከብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ጋር በቅጽበት በመገናኘት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያዎችን (NBE directives) በጠበቀ መልኩ የደንበኞችን ማንነት ማረጋገጥ (KYC) ያስችላል።
የቡና ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ዓለማየሁ በጉዳዩ ላይ እንደገለጹት፤ የቡና ባንክ ዲጂታል ስትራቴጂ ከአገር-አቀፉ የዲጂታል ኢኮኖሚ ጋር የተናበበ መሆኑን ተናግረው በዚህ የዲጂታል ኦንቦርዲንግ አገልግሎት የባንክ አገልግሎትን ለማግኘት እንቅፋት የሆኑትን ጂኦግራፊያዊ እና ሎጂስቲካዊ ገደቦችን ማስቀረት መቻሉን ተናግረዋል። “ይህ አማራጭ የአሰራር መጓተትን በከፍተኛ ደረጃ ከመቀነሱም በላይ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘውን ሀገራዊ የፋይናንስ አካታችነት (Financial Inclusion) ግብ የሚደግፍና እንደ ፋይዳ ካሉ ሀገራዊ የዲጂታል መሰረተ ልማቶች ጋር ለማስተሳሰር፣ የደንበኞችን ማንነት በቅጽበት ማረጋገጥ እና መመዝገብ የሚያስችልም ጭምር ነው” ብለዋል፡፡
የአገልግሎት ስርዓቱ ለህዝብ ክፍት ከመደረጉ በፊት የቅርንጫፍ ሰራተኞች የተሟላ ስልጠና የወሰዱ ሲሆን፣ የመረጃ ታማኝነትን እና ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ የሳይበር ደህንነት (Cybersecurity) ማዕቀፍ ተዘርግቷል። ስርዓቱ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የደንበኞች ፍሰት ለማስተናገድ እና ጥብቅ የሆነ የመረጃ ግላዊነት ስታንዳርዶችን ለመጠበቅ በሚያስችል መንገድ ታስቦ የተነደፈ ነው።
ይህ የዲጂታል ደንበኞች ምዝገባ ስርዓት ከሰኞ ሚያዝያ 26፣ 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለህዝብ ክፍት ሆኖ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
# # #
ስለ ቡና ባንክ፡-
በ2001 ዓ.ም የተመሰረተው ቡና ባንክ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ግንባር ቀደም የግል የንግድ ባንኮች አንዱ ነው። ባንኩ 449 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ አሁን ላይ የ “Vision 2030” ስትራቴጂውን በመተግበር በዲጂታል ፈጠራ እና በእሴት ፍሰት (Value Stream) ላይ በተመሰረተ አሰራር በዘርፉ ቀዳሚ የፋይናንስ ተቋም ለመሆን እየሰራ ይገኛል።
ለተጨማሪ መረጃ፡-
ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንስ ዳይሬክቶሬት
ቡና ባንክ- የባለራዕዮች ባንክ
ስልክ ቁጥር፡-251911403884






