ማርች ፣የዓለምአቀፍ የሴቶች ወርን ምክንያት በማድረግ በባንካችን ዋና መስሪያ ቤት እና በዲስትሪክቶች እየተካሄደ ያለው ደንበኞችን የመጎብኘትና የማመስገን ፣ አዳዲስ ደንበኞችንም የመሳብና የባንኩን አገልግሎቶች የማስተዋወቅ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ተገለጸ፡፡
ከዋናው መስሪያ ቤት ከሚገኙ ልዩ ልዩ የስራ ክፍሎች በተውጣጡ ሴት አባላት የተዋቀረው የማርች 8 የባንክ አገልግሎት ማስተዋወቅና የደንበኞች ጉብኝት ቡድን ከቡና ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ የስራ መመሪያ ተቀብሏል፡፡
መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም በዋናው መስሪያ ቤት በተካሄደው ዝግጅት ላይ ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ ሙሉጌታ አለማየሁ ባደረጉት ንግግር ለሴቶች እኩልነት እና ተሳትፎ እዉቅና ከመስጠት በተጓዳኝ በባንካችን ሁሉም የስራ ክፍሎች በተለያዩ የስራ መደቦች ላይ ያሉ ሴት ሰራተኞች የዓለምአቀፍ ሴቶች ቀንን ምክንያት በማካሄድ ላይ ላሉት ጠንካራ እንቅስቃሴ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ለዚህ የደንበኞች ጉብኝት፣ የባንኩን አገልግሎቶች የማስተዋወቅ እና አዳዲስ ደንበኞችን የመሳብ ተግባርም ምስጋና በማቅረብ ሴት ሰራተኞች ለባንካቸው እድገትና መልካም ስም ግንባታ ላሳዩት ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
በቡና ባንክ በየዓመቱ ሲካሄድ የቆየው ይህ ተግባር እያስገኘ ካለው ውጤት አንጻር ትኩረት ተሰጥቶት በስፋት ሊተገበር ይገባል ያሉት አቶ ሙሉጌታ የባንኩ ከፍተኛ አመራር ለዚህ ተግባር መሳካት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡
“ይህ ተግባር የናንተ ቁርጠኝነትና ጥንካሬ የታየበት ከመሆኑ ባሻገር ከባንካችን እሴቶች አንዱ የሆነው “ትብብር” በስራ የተገለጸበት በመሆኑ ለባንኩ መልካም ስምና እድገት አወንታዊ ድርሻ እንዳለው እናምናለን፡፡ ስለዚህም ከመቼወም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፣ የከፍተኛ አመራሩ ድጋፍም አይለያችሁም” በማለት ኢኒሺየቲቩ የከፍተኛ ማኔጅመንት እውቅና የተሰጠው መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ዘመቻው በዋናው መስሪያ ቤት እና በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ የባንኩ ዲስትሪክቶችና ቅርንጫፎች በሁሉም የሃገራችን ክልሎች ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን ማርች ወር እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ቡና ባንክ ይህንን የማርች ወር ምክንያት በማድረግ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የመንግስት ትምህርት ቤቶች በመገኘት የመማር ማስተማር ሂደቱን ሊያግዙ የሚችሉ መጽሃፍት እንዲሁም ለሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ፓድ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

