Bunna Bank

ጋዜጣዊ መግለጫ |Press release

ቡና ባንክ በአቦል ሞባይል ባንኪንግ ዲጂታል የነዳጅ ክፍያ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ቡና ባንክ በኢትዮጵያ የፋይናንስ እና ቴክኖሎጂ እድገት ጉልህ እርምጃ ያለውን አዲስ የዲጂታል ነዳጅ ክፍያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ። ከትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተቀረጸው አገልግሎቱ ከብሔራዊ የነዳጅ ስርጭት መከታተያ ስርዓት ጋር በመቀናጀት በአገር አቀፍ ደረጃ የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለትን ግልፅነት እና ቅልጥፍና ለማሻሻል የሚያስችል ዘመናዊ የክፍያ አማራጭ ነው ።

ይህ ኢኒሼቲቭ በየጊዜው ተለዋዋጭና ፈጣን ለሆነው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፍላጎት ምላሽ በመስጠት ረገድ ለደንበኞች አስተማማኝ እና ፈጣን የነዳጅ ክፍያ አማራጭን ይዞ የቀረበ አገልግሎት ነው፤ ይህም አገልግሎት ጥሬ ገንዘብ ከመያዝ ጋር የተያያዙ ስጋቶች፣ ግልጽ ያልሆነ ግብይት እና በነዳጅ ማደያዎች ውስጥ የሚስተዋሉ ረጃጅም ወረፋዎችን የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን የሚያግዝ ነው። ስለሆነም ይህ የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት መጀመሩ ቡና ባንክ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የባንክ አገልግሎት ከባቢያዊ ሁኔታን ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።

ደንበኞች ቡና ባንክን ተጠቅመዉ የነዳጅ ግዢን መፈጸም የሚችሉት፤ ከነዳጅ ማደያዉ *820# በመጠቀም ስልካቸዉ ላይ በሚደርሳቸዉ የማረጋገጫ መልእክት፣ አቦል የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ ዉስጥ በመግባት QR ኮድን ተጠቅሞ ስካን በማድረግ ወይም በነዳጅ ማደያው የቀረበውን የማጣቀሻ ቁጥር (Reference Number system) በመጠቀም ነው።

ይህ ባለብዙ አማራጭ ዲጂታል ፕላትፎርም በማንኛውም አይነት ሞባይል ስልክ እንዲሁም በኢንተርኔት ወይንም ያለኢንተርኔት በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ ሁሉም ደንበኞች ሰፊና ተደራሽ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። አገልግሎቱ የተሻሻለ የክፍያ አማራጭን በማቅረብ የአሽከርካሪዎችን ፍላጎት ያሟላ ሲሆን ለነዳጅ ማደያዎች ደግሞ ስራቸውን ፈጣንና ቀልጣፋ እንዲሆን ያግዛቸዋል፤ በተጨማሪም የመንግስት አካላትን የቁጥጥር ስርዓት በማሻሻል ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ ይጠበቃል።

ባንኩ በተወሰኑ የተመረጡ የነዳጅ ማደያዎች የጀመረውን ይህን አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ ከሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ጋር በመተባበር  ለማስፋፋት አቅዷል፡፡ ቡና ባንክ  የኢትዮጵያን የባንክ መሠረተ ልማት የማዘመን እና አስፈላጊ አገልግሎቶችን ዲጂታል የማድረግ ብሔራዊ ጥረቶችን ለመደገፍ ተልእኮውን አንግቦ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ባንኩ ከዲጂታል ነዳጅ ክፍያ በተጨማሪ በመላ አገሪቱ ቀልጣፋ እና ተደራሽ አገልግሎትን በስፋት ለማቅረብ ለያዘው ዕቅድ ደህንነታቸው የተጠበቀ እና እየሰፉ የሚሄዱ የተለያዩ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶች ላይ ኢንቨስት ማድረጉን ቀጥሏል።

ደንበኞች የነዳጅ ክፍያ አገልግሎቱን ለመጠቀም በቅድሚያ የቡና ባንክ ሞባይል ባንኪንግ አገልግሎትን መመዝገብ ያለባቸዉ ሲሆን በመቀጠል በመረጡት አማራጭ ክፍያቸዉን መፈፀም ይችላሉ፡፡ ደንበኞች ለተጨማሪ መረጃ 8501 ላይ በመደወል የደንበኞች አገልግሎት ሰራተኞችን ማነጋገርና መረጃ ማግኘት ይችላሉ።

ቡና ባንክ ከ14ሺህ በላይ የሚሆኑ ባለአክሲዮኖች ያሉት ከ15 ዓመታት በፊት የተቋቋመና 454 በሚሆኑ ቅርንጫፎቹ በኢትዮጵያ ሁሉም ክልሎች አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ የባለራዕዮች ባንክ ነው፡፡ ባንካችን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አቅም ያገናዘበ ልዩ ልዩ የቁጠባና ብድር አገልግሎቶችን በማቅረብ ተዓማኒነትን አትርፏል፡፡

ሐምሌ 21-2017

በቡና ባንክ ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽንና ፕሮሞሽን ዋና ክፍል የተዘጋጀ

2 thoughts on “ጋዜጣዊ መግለጫ |Press release”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This will close in 0 seconds

You cannot copy content of this page